Wednesday, December 29, 2010

ወግእዝ ነገሩ...ትዝታ-ቢጤ

ባለፈው ክታባችን ወደሰዋሰው እየተንደረደርን እንደኾነ ጠቁመን ነበር። ኾኖም አገባቡን ከመጀመራችን በፊት የንባቡን ትምርት ደማ እንድናደርገው  በቅርብ ካገኘናቸው ወዳጆች በቀረበልን አስተያየት መሠረት መልሰን ለጥቂት ጊዜ ንባቡ ላይ ልናተኩር ዐስበናል። 

አንድ ትዝታ-ቢጤ ግን ጣልቃ እናስገባ፦

ከዚህ ምክታብ ርእስ ሥር ያስቀመጥነው ጥቅስ ለቅዱሳት መጻሕፍት አንባቢዎች ኹሉ የሚያስታውሰው ተመሳሳይ ነገር አለ፤ ለዚች ገጽ መጋቢ ደግሞ አንድ ልዩ ትዝታ ይዟል። እናካፍላችኹ። ይህ ደቅ/መርድእ (ተማሪ) ባንድ ወቅት የሮማውያንን ቋንቋዎች ታሪክ እና ባሕርይ ለመረዳት ሽቶ  ባንድ ያውሮፓ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ የሊህን ቋንቋ ቤተሰብ የሚያስተዋውቅ ኮርስ መከታተል ይጀምራል። ፕሮፌሰሯ ከኹሉ አስቀድማ አባል ቋንቋዎቹን ስትዘረዝር ፓፒያሜንቱ የሚባለውን፤ የፖርቱጊዝ ቅኝ የነበሩ አፍሪቃውያን የፈጠሩት ቋንቋ በመጨረሻ ላይ ጠቀሰች። በቀጣዩ ክፍለ-ጊዜ የቋንቋዎቹ ድምፅ ምን ምን እንደሚል ግንዛቤ ለማስጨበጥ በማሰብ  አንድ ምንባብ በቴፕ ታሰማለች፤ ተራ በተራ፦ በላቲን፣ በፈረንሳይኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በስፔንኛ... መጨረሻ ላይ (በምንኛ ሊኾን ነው? ገምቱ እስኪ) በፓፒያመንቱ። እዚህ ደርሳ ድምፁ ሲሰማ፤ በክፍሉ ውስጥ የነበረው ብቸኛ አፍሪቃዊ ያ ደቅ/መርድእ ስለነበረ፤ ፕሮፌሰሯም፣ ተማሪዎቹም ወደርሱ ዘወር ብለው እንደመሳቅ ካሉ በዃላ  እነርሱ ስለርሱ አፍረውለት ባዘኔታ ተመለከቱት።

የሚገርመው (ምናልባትም የማይገርመው) ያ ምንባብ ዘፍ ፲፩ ነበር። ደግነቱ ያ መርድእ ይህንን ጥቅስ ባገሩ ሳለ ሲማረው፦ '"ወአሐዱ ነገሩ" ባለው "ወግእዝ ነገሩ" የሚል አብነት ይገኛል።'  ተብሎ ሲታተት ሰምቶ ኖሯል (ይህም፦ 'where it says  "of one language" there is another version that says "of the First/Geez Language"' ማለት ነው)። ስለዚህም የርሱ ቋንቋ የቋንቋዎች ኹሉ አባት፣ ቊንጮ ቢኾን እንጂ  ሙጣጫቸው፣ ልሳሻቸው ስላይደለ፤ ኩራት ኪሰማው በቀር ሊታፈርለት፣ ሊታዘንለት የማያሻው እንደኾነ በማወቁ ደስ ፈቅ አለው (ፈጽሞ ደስ  አለው)። ፕሮፌሰሯ እና ሌሎቹ ተማሮች ግን እንደመገረም ብለው ነበር፤ በነርሱ ቤት መሳቀቅ ሲገባው የኩራት ፈገግታ በማሳየቱ። እኽ... ግን ምን ይደረጋል... ያኔ ብቻውን ነበር...

ዛሬስ?

Saturday, December 11, 2010

ትምህርተ-ግእዝ ለአእምሮ

ከዚህ ገጽ በስተቀኝ በኩል ባለው የ"እንኳን ወደዚህ አመጣችኹ" (እንቋዕ አብጽሐክሙ ዝየ) አጭር የአቀባበል መልእክት እንደጠቆምነው፤ የግእዝ ትምርት ኹለት መንገድ አለው... ስለኾነም ባለፉት ክታቦቻችን ብዙ ዐተታ ሳናትት ንባብ እና ጥፈትን የሚመለከቱ መልመጃዎችን አከታትለን አቅርበናል። የንባብ እና የጥፈት ጓዝ ገና ብዙ የሚቀረው ቢኾንም፤ እየቀደም የምንቀጥልበት ኾኖ ሰዋስውን ለመጀመር እየተንደረደርን ነው። ስላቀራረባችን በመጠኑ እንደተናገርነው ስለዐላማችንም ጥቂት በመጠቆም።

"ግእዝ በመሥመር ላይ" ዐላማዋ ባጭሩ፦ "በገዛ ዳቧችን ልብ ልቡን እንዳጣነው" እንዳንቀር ለማድረግ ነው። ይኸውም ግእዝን ቢኾንልን እንድንሰማው፣ እንድንናገረው፣ እንድናነበው፣ እንድንጽፈው ለማስቻል፤ ባይኾንልን እንኳ "ጠዐሙ ወታእምሩ" (ቀምሳችኹ ዕወቁ፣ ተረዱ) ነውና እውነተኛ ጣዕሙን ቀምሰን በምር (በቁም ነገር፣ ዋዛ በሌለበት፣ ግዴታን በሚያስከትል)
በእሙር/እሙረ (በታወቀ፣ በተረዳ ነገር) እንድናከብረው እና ከትውልድ ወደትውልድ እየፋፋ እየተስፋፋ እንዲኼድ የየበኵላችንን ድጋፍ እንድናደርግለት (ለምሳሌ፦ ልጆቻችን እንዲማሩት አስፈላጊ ኹኔታዎችን በማመቻቸት--በግል፣ በማበር፣ በመንግሥት ደረጃ)፤ ያለውድ በግድም ይኹን ያለግድ በውድ ባማርኛም ኾነ በሌሎች ያገራችን ቋንቋዎች ውስጥ ስናገኘው ደግሞ ባግባቡ እንድንጠቀመው ለማነሣሣት ነው።

እኛ የገዛ ዳቧችንን ልቡን አጥተን በአእምሮ ረ
ብ ስንሣቀይ፤ ሌሎች ቊንጣን እስኪይዛቸው ድረስ እየተመገቡት "በላዕነ ወጸገብነ"ን ይዘምራሉ። እስኪ እነርሱ የሚሉንን ሰምተን እንኳ ልብ እንግዛና የዳቧችንን ልብ ልቡን ከማጣት ርግማን ራሳችንን እናድን። እንዲያው ለምሳሌ ያኽል፦ አንድ የኢትዮጵያን ምድር በካርታ ከማየት በቀር በእግሩ ረግጧት እንኳ ሳያውቅ የግእዝ ተጠቃሚ--እንዲያውም አሳላፊ--ለመኾን የበቃ ምሁር ስለግእዝ ከተናገረው ቁምነገር እናቅምሳችኹ፦
  • ...die so lange vernachlässigte äthiopische Grammatik denen der anderen semitischen Sprachen ebensoviel Licht bringt, als sie von ihnen empfängt.
  • ይህን ያኽል ዘመን ችላ ተብሎ የኖረው የግእዝ ሰዋስው ለሌሎች ሴማውያን ቋንቋዎች[ለዐረብ እና ለሱርስት፣ ለዕብራይስጥ እና ለመሳሰሉት ማለቱ ነው] የሚያመጣላቸው ብርሃን ርሱ ከነርሱ ከሚቀበለው ቢበልጥ እንጂ አያንስም።
እንዲህም ስለኾነ ብሎ፤ ከዚያው በማያያዝ ይቀጥላል (የህንን ነው ልብ ማለት)፦
  • Auch das Volk, ...mit starker Geistes- und Denkkraft ausgerüstet gewesen sein.
  • ሕዝቡም እንጂ፣ ሕዝቡም እኮ... እጅግ ጠንካራ መንፈሳዊ/የአእምሮ እና ኅልያዊ/የማሰብ ይልን የታጠቀ ነበር።
የሚቆጨው፤ የሚከነክነው፤ እጅግ የሚያሳዝነው፤ ያ ትጥቅ መፈታቱ ነው!!! አልፈታነውም ብለን እንዳንዋሽ። ይልቅ መልሰን እንታጠቀው ብሎ ቆርጦ መነሣት ይሻለናል።

እንግዲህ የእኛም ዐላማ ይኸው ነው:-
የአእምሮ እና የሊ ዝናራችንን መልሶ ለመታጠቅ መጣር፤ ሌላው ቢቀር ሕይወታችንን ለመጠበቅ፣ ራሳችንን ለመረዳት ስንል። "መንፈስን"/"አእምሮ"ን (spirit/mind) እና "ኅሊ"ን/"ሐሳብ"ን (thought) በተመለከተ አንዳችንም አንዳችን የየራሳችን ፍልስፍና እንደሚኖረን ግልጽ ነው። እንዲያውም ያንዳችንን ካንዳችን ብናነጻጽረው ምናልባት ሰማይና ምድር ሊኾን ይችላል። የኛ ነጥብ የሚያተኩረው ግን (በግል የሚኖሩንን ልዩነቶች ባንዘነጋም) በዘውዱ ከሚመካ ንጉሥ ባመዱ እስከሚያድር ድኻ ያለነው ኢትዮጵያውያን በምንዋኝበት "የጋራ አምሳለ-ሊና" (social imaginary) ላይ እንጂ (ለጊዜው) በ"ታኦርያ"/በትወራ ደረጃ (at the level of theory) ስለሚያከራክር ጕዳይ አይደለም። ይህ ደግሞ--ማለትም፤ የጋራ አምሳለ-ሊናችን--ባብዛኛው በግእዝ መሠረት ላይ የጸና እንደነበረ፤ አኹንም ጥልቀቱን እንለካ ብንል መለኪያው ከዚያ እንደማያልፍ አሌ ሊባል አይችልም። አይችልምና፤ የግእዝ ተፈላጊነት ወለል ብሎ ይታያል።

Thursday, December 9, 2010

አ(ስ)ቀራረብ

ወደፊት ከመግፋታችን በፊት ስለአ(ስ)ቀራረባችን ጥቂት እንግለጥ። 'የምን ማስቀራረብ ነው ደግሞ?' የሚል ዐሳብ የወደቀበት እንዳለ፤ እዚሁ ጥቂት ዐረፍ ብሎ ቃሉን በማመላለስ ያስብ። ከቻለ ከግእዙ ጀምሮ ወዳማርኛው፤ አለያም ካማርኛው ጀምሮ ወደግእዙ ያቅና፤ ካልኾነለትም ዐማርኛውን ብቻ ያሰላስለው... እንግልጣሩም (እንግሊዝኛውም) ያግዛል...

(ቀርበ = ቀረበ፤ አቅረበ = አቀረበ፣ አስቀረበ፤ ተቃረበ = ተቀራረበ፤ አስተቃረበ = አቃረበ፣ አቀራረበ...)

ምንም ይኹን ምን ነገርዮው ራሱ ሲቀርብ፣ ሲጠጋ "ቀርበ፣ ቀረበ" ([he/(she)/it] present(ed) [oneself]) ወይም ([he/(she)/it]) approach(ed)) እንላለን። አንዱ ሌላውን ሲያቀርበው ሲያስጠጋው ወይም እንዲቀርብ እንዲጠጋ ሲያደርገው ደግሞ "አቅረበ፣ አቀረበ/አስቀረበ" ([he/(she)/it] present(ed) [something/someone else] / [he/(she)/it] re-present(ed)) ወይም ([he/(she)/it]) let (something/someone else) approach) እንላለን። ስለዚህም፤ አ(ስ)ቀራረብ = presentation (in the sense of: the way of presenting something/someone/oneself) ወይም = approach (in the sense of: the way of letting something/someone/oneself approach)

ግእዝ እንዲቀርበን፣ እንዲቀርብልን ለማድረግ፤ ግእዝን ሊአቀርብልን፣ ሊአስቀርብልን እየተሰናዳ ያለው ትምርት አካኼዱ--አቀራረቡ፣ አስቀራረቡ--እንዴት ነው? ይህ ትምርት፦ ግእዝ እንዴት ኾኖ፣ በምን መልክ እንዲቀርበን፣ እንዲጠጋን ለማድረግ እየተሰናዳ ነው? ዝግጅቱ የሚያቀርበውን የሚያቀርበውስ ለማን ነው? ለደቂቅ ወይስ ለልሂቅ፣ ለወጣኒ ወይስ ለማእከላዊ? ለቀዳሽ ወይስ ለሰባኪ፣ ለቋንቋ ተማሪ ወይስ ለደራሲ፣ ለገጣሚ ወይስ ለጋዜጠኛ፣ ለሐኪም ወይስ ለመሐንዲስ፣ ለዘፋኝ ወይስ ለፖለቲከኛ ፣ ለባለርስት ወይስ ለስደተኛ...? እንደወረደ ወይስ መላልሶ ከላልሶ፣ ደረጃ በደረጃ...?

እሊህን እና እሊህን የመሳሰሉ ነገሮችን ማሰባችን አልቀረም ነበር፤ ባንዱም ባንዱ የጥያቄ ተርታ ግን ለዚህኛው ብለን ለመወሰን ተቸግረናል። ምክንያቱም በመሥመር ላይ ውለው ትምርቱን ለመከታተል እንደሚችሉ የምንገምታቸው ተጠቃሚዎች "ጥንተ-ጸወን"/"ጥንተ-መሠረት" (background) የተለያየ በመኾኑ ነው። የኾነው ኾኖ፤ ለጊዜው ዐቅማችን እንደፈቀደ ባንዱም ባንዷ ግእዝን የመማር ፍላጎት በሚያነሣሣ እና በሚያጠናክር መልኩ እንጀምረውና አንዱም አንዷ እንደየግል ችሎታ እና ፍላጎታቸው አፍኣ-መሥመርም ጭምር (off-line) እንዲማሩት ለማበረታታት እንሞክራለን። ስላ(ስ)ቀራረባችን ዐሳብ ሊሰጠን የሚሻ ቢኖር በደስታ እንቀበላለን። በማስተማር ለመሳተፍ የሚሻ ቢገኝ'ማ ፦ ንተሐሠይ ጥቀ።

Wednesday, December 8, 2010

በእንተ-ሥርዐተ-ጽሕፈት (የቀጠለ)

ባለፈው ክታብ (ፖስት) የተወሰኑ የግእዝ ፊደላት አደጋ ላይ እንዳሉ እና አነሱን መታደግ ካልቻልን፤ የቀሩትም ቢኾኑ ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚገጥማቸው አመልክተን ነበር። እና ምን እናድርግ የምንል ከኾነ፤ በመጀመሪያ ደረጃ፤ በምር እናስብ፣ በምር እንጠይቅ። እንዲያው ዝም ብለን በግዴለሽነት "ምን ይደረግ፣ ምን ይኹን?" ማለት ሳይኾን፤ ምን እናድርግ (እኛ)? ምን ላድርግ (እኔ)? ብለን እንጠይቅ። ጠይቀንም መተው ሳይኾን እናስብበት። እንዲህ ከኾነ ላንዳችንም ላንዳችን የሚገለጥልን ቀና ነገር ይኖራል። እንዲህ የሚገለጥልንንም በጎ ነገር በውይይት አጠናክረን የተግባር አግጣጫ መንደፍ እንችላለን።

እንዲያው ተግባራዊ ነገር ሳንጠቁም ላለማለፍ፤ እስኪ አንድ በጣም ቀላል ነገር እንፈጽም። ቃል እንግባ። እነዚያን አደጋ ላይ ናቸው ያልናቸውን ሆህያት ባለማወቃችን ካልኾነ በቀር እያወቅን እንዳንጨቁናቸው። ይልቁንም ሙያቸውን እየተማርን እንድንጠቀማቸው። በሉ ቃል ከገባን ከዚህ ክታብ (ፖስት) ጋራ ተሳስሮ በቀረበው ሰነድ መጨረሻ ገጽ ላይ የምናየውን ዐዋጅ በተግባር ለመተርጎም እንሞክር (እንደተለመደው የክታቡን ርእስ (the title of this post) ስትኮረኩሙ ታገኙታላችኹ)።

Tuesday, December 7, 2010

በእንተ-ሥርዐተ-ጽሕፈት

ግእዝን በመሥመር ላይ ልናጎማልለው ስንጀምር፤ መሥመሩ የሚዘረጋበትን ሰሌዳ የፈተንነው (የሞከርነው) ፊደላቱን በመለጠፍ ነበር። ስለፊደላቱ ግን ምንም አላወሳንም፤ ብዙ መናገር የሚቻል ኾኖ ሳለ። አኹንም ብዙ ለማውሳት አላሰብንም። ነገር ግን የግእዝ ጥፈቱ ያለሆህያቱ ሊታሰብ አይችልምና፤ እስኪ ፊደልን በተመለከተ በቅጥነተ-ልብ ሊታሰብበት የሚገባ አንድ ነገር እናንሣ።

ረ ቆዩ ከዚያ በፊት፦ ግእዝ የማን ቋንቋ ነው? ግእዝ የየትኛው ቋንቋ ቤተሰብ ነው?

ልብ በሉ፦ እነዚህ ጥያቄዎች አንድ ናቸው፣ አንድ አይደሉምም። አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ግእዝ-ነክ ጥያቄ መኾናቸው ነው። ልዩ የሚያደርጋቸው ደግሞ፤ የመጀመሪያው ጥያቄ የሚያተኩረው፦ ግእዝ በቋንቋነቱ የማናቸውም ቋንቋዎች ቤተሰብ ቢኾንም ባለቤቶቹ እነማን ናቸው የሚለው ቊምነገር ላይ ነው፤ ኹለተኛው የሚመለከተው ግን፦ የቋንቋው ባለቤቶች አነማንም ይኹኑ እነማን፤ ግእዝ በቋንቋነቱ ከየትኞቹ "አብያተ-ልሳን" (የቋንቋ ቤተሰቦች) ይመደባል የሚለውን ጥያቄ ነው።

መልሱ አንድ ነው፤ ኹለት ገጽታዎች ያሉት፦ ግእዝ በከናፍረ-ኵሽ ውስጥ ተመቻችቶ የሚኖር 'ሴማዊ' ልሳን ነው። አንዳንድ (ኵሻዊም ሴማዊም ኦማዊም ያይደሉ) አስናነ-ባዕድ (የባዕድ ጥርሶች) በየዋሃን ድድ ውስጥ ተሰክተው እየነከሱት ከሚሰቃይ በቀር።

እንዲህም ስለኾነ ግን 'ግእዝ ሴማዊ ነውና ለኵሻውያን ምናቸውም አይደለ' ለማለት አይቻልም፤ መቸም መች ቢኾን ኵሻውያንን-አልቦ ግእዝ ተናጋሪ በታሪክ አይገኝምና።... በዚህ ጕዳይ ላይ በሌላ ጊዜ ብንመለስበት ይሻላል። ባጭሩ ግን፦ የግእዝ ባለቤት ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ነው። ልብ በሉ፦ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ነው ያልነው፤ ከሰሜን እስከደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከምዕራብ--መናገሩን ቢችለውም ባይችለውም!

የቋንቋ ቤተሰብን በተመለከተ፤ ግእዝ 'ሴማዊ' ወይም 'ደቡብ ሴማዊ' ነው ለማለት ይቻል ይኾናል፤ በጠይሙ። ነገር ግን "ወአሐዱ (ወግእዝ) ነገሩ ለኵሉ ዓለም" በሚለው የቅዱስ መጽሐፍ መሠረት ስንኼድ፤ የኹሉ ቋንቋ ቤተሰቦች አባት እንደነበረም እናያለን። ቢያንስ ቢያንስ የቋንቋ ጠበብት "ጕንደ-ልሳናት ሴማውያን" (Proto-Semitic) የሚሉት ቅሉ ግእዝ ነው ሊያሰኙ የሚችሉ ነገሮች አሉ። ከላይ እንዳልነው ጕዳዩ ሰፊ ስለኾነ ለጊዜው ይቆየንና ስለፊደል አንድ ዐሳብ እንሰንዝር።

አስቀድመን ጠቆም ያደረግናቸው "አስናነ-ባዕድ" ሊያደቋቸው ሊያጠፏቸው የሚሿቸውን ፊደላት ሕይወት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይሻል፣ ምን ማድረግ ይገባ፣ ምን ማድረግ ይቻል ይኾን? እሊህ "አስናነ-ባዕድ" ዐላማቸው የግእዝን ፊደል በጠቅላላ ማጥፋት ነው። አካኼዳቸው ግን አንድ ባንድ ስለኾነ፤ ደከም ያሉትን በመግደል ነው የሚጀምሩት፦ እነ ሐ፣ ኀ፣ዐ፣ ሠ፣ ጸን እንዲሁም ደግሞ አነጐ፣ ኈ፣ኰ፣ ቈን ከነውሉደ-ውሉዳቸው። ስለዚህ ጎበዝ፦ ዳሩ ሲወረር መኻሉ ዳር እንደሚኾን አንዘንጋ! እናስ? የምትሉ ከኾነ፤ እና'ማ... (ኦ! እኩለ-ሌሊት አልፏልና፤ ሌላ ጊዜ እንመለስበት)

ምልማደ-ንባብ (የንባብ መልመጃ) -3

ለቅምሻ ለመነሻ ያኽል ያዘጋጀናቸውን የምንባብ መልመጃዎች በ"አቡነ ዘበሰማያት" ማሠራችን ነው (እንደተለመደው ርእሱን ስትኮረኩሙት ታገኙታላችኹ)። የንባቡ ትምርት ተጠቃሚ መኖር አለመኖሩን፣ ዘዴውም ተስማሚ መኾን አለመኾኑን ገምግመን ወደፊት እንቀጥልበት ይኾናል።

ለጊዜው ግን ስለ"ጥፈት"ም እንዲሁ የምንችለውን ከዚህ በመቀጠል ቀመስ እናደርግና ወደ"አገባቡ" እና ወደ"አግባቡ" እንገሠግሣለን።

Sunday, December 5, 2010

ምልማደ-ንባብ (የንባብ መልመጃ) -2

አኹንም "ምልማደ-ንባብ (የንባብ መልመጃ) -2" የሚለውን የዚህኛውን ልጥፍ (ፖስት) ርእስ ይኮርኵሙና የሚከፈትልዎን ከዘወትር ጸሎት የተወሰደ ባለምልክት ንባብ መላልሰው ይለማመዱ።

መልመጃው በጥንተ-ተፈጥሮው በተለይ ለጃማይካውያን ታልሞ የተዘጋጀ ስለነበረ፤ አነባበቡን በሮማይስጥ ፊደልም ጭምር ለማሳየት ተሞክሯል። ይኸም ከሚጠቅም በቀር የሚጎዳው ነገር እንደሌለ ስለገመትን ገንጥሎ ማስቀረት አያስፈልግም በሚል እንዳለ አያይዘን አቅርበነዋል።