Saturday, December 11, 2010

ትምህርተ-ግእዝ ለአእምሮ

ከዚህ ገጽ በስተቀኝ በኩል ባለው የ"እንኳን ወደዚህ አመጣችኹ" (እንቋዕ አብጽሐክሙ ዝየ) አጭር የአቀባበል መልእክት እንደጠቆምነው፤ የግእዝ ትምርት ኹለት መንገድ አለው... ስለኾነም ባለፉት ክታቦቻችን ብዙ ዐተታ ሳናትት ንባብ እና ጥፈትን የሚመለከቱ መልመጃዎችን አከታትለን አቅርበናል። የንባብ እና የጥፈት ጓዝ ገና ብዙ የሚቀረው ቢኾንም፤ እየቀደም የምንቀጥልበት ኾኖ ሰዋስውን ለመጀመር እየተንደረደርን ነው። ስላቀራረባችን በመጠኑ እንደተናገርነው ስለዐላማችንም ጥቂት በመጠቆም።

"ግእዝ በመሥመር ላይ" ዐላማዋ ባጭሩ፦ "በገዛ ዳቧችን ልብ ልቡን እንዳጣነው" እንዳንቀር ለማድረግ ነው። ይኸውም ግእዝን ቢኾንልን እንድንሰማው፣ እንድንናገረው፣ እንድናነበው፣ እንድንጽፈው ለማስቻል፤ ባይኾንልን እንኳ "ጠዐሙ ወታእምሩ" (ቀምሳችኹ ዕወቁ፣ ተረዱ) ነውና እውነተኛ ጣዕሙን ቀምሰን በምር (በቁም ነገር፣ ዋዛ በሌለበት፣ ግዴታን በሚያስከትል)
በእሙር/እሙረ (በታወቀ፣ በተረዳ ነገር) እንድናከብረው እና ከትውልድ ወደትውልድ እየፋፋ እየተስፋፋ እንዲኼድ የየበኵላችንን ድጋፍ እንድናደርግለት (ለምሳሌ፦ ልጆቻችን እንዲማሩት አስፈላጊ ኹኔታዎችን በማመቻቸት--በግል፣ በማበር፣ በመንግሥት ደረጃ)፤ ያለውድ በግድም ይኹን ያለግድ በውድ ባማርኛም ኾነ በሌሎች ያገራችን ቋንቋዎች ውስጥ ስናገኘው ደግሞ ባግባቡ እንድንጠቀመው ለማነሣሣት ነው።

እኛ የገዛ ዳቧችንን ልቡን አጥተን በአእምሮ ረ
ብ ስንሣቀይ፤ ሌሎች ቊንጣን እስኪይዛቸው ድረስ እየተመገቡት "በላዕነ ወጸገብነ"ን ይዘምራሉ። እስኪ እነርሱ የሚሉንን ሰምተን እንኳ ልብ እንግዛና የዳቧችንን ልብ ልቡን ከማጣት ርግማን ራሳችንን እናድን። እንዲያው ለምሳሌ ያኽል፦ አንድ የኢትዮጵያን ምድር በካርታ ከማየት በቀር በእግሩ ረግጧት እንኳ ሳያውቅ የግእዝ ተጠቃሚ--እንዲያውም አሳላፊ--ለመኾን የበቃ ምሁር ስለግእዝ ከተናገረው ቁምነገር እናቅምሳችኹ፦
 • ...die so lange vernachlässigte äthiopische Grammatik denen der anderen semitischen Sprachen ebensoviel Licht bringt, als sie von ihnen empfängt.
 • ይህን ያኽል ዘመን ችላ ተብሎ የኖረው የግእዝ ሰዋስው ለሌሎች ሴማውያን ቋንቋዎች[ለዐረብ እና ለሱርስት፣ ለዕብራይስጥ እና ለመሳሰሉት ማለቱ ነው] የሚያመጣላቸው ብርሃን ርሱ ከነርሱ ከሚቀበለው ቢበልጥ እንጂ አያንስም።
እንዲህም ስለኾነ ብሎ፤ ከዚያው በማያያዝ ይቀጥላል (የህንን ነው ልብ ማለት)፦
 • Auch das Volk, ...mit starker Geistes- und Denkkraft ausgerüstet gewesen sein.
 • ሕዝቡም እንጂ፣ ሕዝቡም እኮ... እጅግ ጠንካራ መንፈሳዊ/የአእምሮ እና ኅልያዊ/የማሰብ ይልን የታጠቀ ነበር።
የሚቆጨው፤ የሚከነክነው፤ እጅግ የሚያሳዝነው፤ ያ ትጥቅ መፈታቱ ነው!!! አልፈታነውም ብለን እንዳንዋሽ። ይልቅ መልሰን እንታጠቀው ብሎ ቆርጦ መነሣት ይሻለናል።

እንግዲህ የእኛም ዐላማ ይኸው ነው:-
የአእምሮ እና የሊ ዝናራችንን መልሶ ለመታጠቅ መጣር፤ ሌላው ቢቀር ሕይወታችንን ለመጠበቅ፣ ራሳችንን ለመረዳት ስንል። "መንፈስን"/"አእምሮ"ን (spirit/mind) እና "ኅሊ"ን/"ሐሳብ"ን (thought) በተመለከተ አንዳችንም አንዳችን የየራሳችን ፍልስፍና እንደሚኖረን ግልጽ ነው። እንዲያውም ያንዳችንን ካንዳችን ብናነጻጽረው ምናልባት ሰማይና ምድር ሊኾን ይችላል። የኛ ነጥብ የሚያተኩረው ግን (በግል የሚኖሩንን ልዩነቶች ባንዘነጋም) በዘውዱ ከሚመካ ንጉሥ ባመዱ እስከሚያድር ድኻ ያለነው ኢትዮጵያውያን በምንዋኝበት "የጋራ አምሳለ-ሊና" (social imaginary) ላይ እንጂ (ለጊዜው) በ"ታኦርያ"/በትወራ ደረጃ (at the level of theory) ስለሚያከራክር ጕዳይ አይደለም። ይህ ደግሞ--ማለትም፤ የጋራ አምሳለ-ሊናችን--ባብዛኛው በግእዝ መሠረት ላይ የጸና እንደነበረ፤ አኹንም ጥልቀቱን እንለካ ብንል መለኪያው ከዚያ እንደማያልፍ አሌ ሊባል አይችልም። አይችልምና፤ የግእዝ ተፈላጊነት ወለል ብሎ ይታያል።

1 comment:

 1. ምንት ንብል ለዝንቱ ሰናይ ነገር ፡፡
  አምላከ ቅዱሳን አምላክነ ይትባረክ፡፡
  ጥቀ ተፈስሐት ነፍስየ፡፡በአማን አልብየ ቃል ለፍስሐየ፡፡
  ሰናይ ወጠንክሙ ፡፡ይኩን ምስሌክሙ ዘአወጠነክሙ፡፡

  ReplyDelete