Friday, May 6, 2011

ዘር እና ነባር

[የንባብ መልመጃዎችን ማቅረባችንን እንቀጥላለን። ነገር ግን የድመፅ እና የሳሕሳሒ/የአንሳሕሳሒ (የተንቀሳቃሽ) ምሥል መዝገቦችን እያይዘን ለማቅረብ ያጫጫናቸውን ስልት እስክንችልበት ድረስ ታገሱን። እስከዚያው ዝም ከምንል አገባቡን/ሰዋስዉን እንጀምረው፦ በነገር፡)]   አ.ኪ.ወ.ክ.


"ነገር" የሚለው ቃል ትርጕም ምንድር ነው? "ነገር" ቅሉ "ምን ነገር" ነው? (What, or what kind of, thing/entity is thing/entity as such?) የነገር "እነቱ" (its Being) ምንድር ነው?

በፍጥረትም በሥነ-ፍጥረትም፤ ወይም በሌላ አነጋገር በህላዌም በንባበ-ህላዌም፤ ከ“ነገር” ሌላ ኹሉን ጠቅላይ ኹሉን ወካይ “በቂ” የሚገኝ አይመስለንም። በቋንቋም እንዲኹ። ቋንቋ ቅሉ “ነገር” መባሉ በከንቱ አይደለም። ነገረ-ዕብራይስጢ (Hebraic Language)፣ ነገረ-ዮናኒ(Greek Language)፣ ወዘተርፈ እንዲል።

እንዲህም ስለኾነ ነገርን ለማብራራት ከነገር በላይ ሌላ ነገር ማምጣት ችግር ነው። ረ ጭንቅ ነው። ቢቻልም ስንኳ፤ የሚሞከረው እንዲህ ባለ ክታብ አይደለም። ስለዚህ ነገርን ከውጭ ለመያዝ ለመጨበጥ ከመጣር ይልቅ በውስጡ ያለውን የዐይነት ልዩነት መተንተኑን እንያያዝ። 

በግእዝ ሊቃውንት የቋንቋ ልበማ ኹለቱ ዐበይት የነገር ዐይነቶች () ዘር እና () ነባር ናቸው። አንዱን ያንዱ ንኡስ ስብስብ ለማድረግ በሊቃውንቱ መካከል በሚደረገው ክርክር፤ ዘርን ጠቅላይ ነባርን ንኡስ የሚያደርጉት እና ነባርን ጠቅላይ ዘርን ንኡስ የሚያደርጉት በቁጥር ምን ያኽል እንደሚበላለጡ ካለማወቃችን ባሻገር፤ በነጥብ ደረጃም ለመሰለን እናደላ እንደኾነ እንጂ፤ ትክክሉ ይኸኛው ነው ብሎ ለመፍረድ የሚያስችል ዐቅም የለንም።

ኹንና ለጊዜው አንድ ቁም ነገር ጠቁመን እንለፍ፦ ግእዛዊ አእምሮ ዓለሙን የሚያይበትን ምቅዋም (perspective) ለማግኘት የቋንቋውን አገባብ ብቻ ሳይኾን የባለቤቶቹን የሥነ-ፍጥረት/ንባበ-ህላዌ ዐተታዎች (ontological inquiries) ጭምር በቅጥነተ-ልብ መመልከት ያስፈልጋል።


 "ዘር፣" "ነባር" ማለት ምን፣ ምን ማለት እንደኹኑ በቀጣይ ክታባችን እናያለን... ይቆየን።

Tuesday, April 26, 2011

እንቋዕ አብጽሐክሙ = ዕሠይ፣ እንኳዕ አደረሳችኹ!

በዐማርኛ የ"እንኳ"/የ"ስንኳ፣" እና  የ"እንኳን"/የ"ስንኳን" ያፈታት ስልታቸው ብዙ ነው። የማበላለጥና የማላላቅ፣ የማማረጥና የማሻሻል፣ የማዋረድና የማሳነስ ቃል ይኾናሉ።  የግእዝ አቻዎቻቸው "ጓ፣" "ጥቀ" ወይም "አኮ" ሊኾኑ ይችላሉ።

ምሳሌ፦
  • የፈጣሪን ባሕርይ ሰው ይቅርና መልአክ እንኳ/ስንኳ አያውቀውም። (...ይትርፍሰ ሰብእ መልአክኒ ጥቀ...)
  • እንኳን/ስንኳን ጠላና ይቀራል ጠጅ፤ እንዲያው ነገሩ ይቆጫል እንጅ። (ጥቀ "ጽሙቅ" (ጠላ) ይተርፍ ምዩስ/ሜስ (ጠጅ)...)
  • አንተም እንኳ/ስንኳ እንደኛ ወጥመድ ገባኽ (ጠፋኽ)። (አንተሂ ተሠገርከ ከማነ።)
  • እንደሱ እንኳን አይደለም። (አኮ ከማሁ)
አለቃ ደስታ "ስንኳ፣ ስንኳን የካህናት፤ እንኳ፣ እንኳን የሕዝብ አነጋገር ነው" ይላሉ። እሊህን በዚሁ እንለፋቸውና "እንቋዕ" (እንኳዕ/እንኳን) ምን ማለት እንደኾነ ባጭሩ ተናግረን ወደሰላምታችን እንኺድ።

በተለምዶ "እንኳን" ብንለውም "እንኳዕ" የሚለው ቃል ከ"እንቋዕ" እንደተገኘ ብዙ ማብራሪያ አያሻውም። በግእዝ "እንቋዕ" የሚባለውም "ንኡስ አገባብ" የደስታ ቃል ነው። "እንኳ፣ እንኳዕ፤ ዕሦ፣ ዕሠይ፤ ወሰው፣ ውሽን፤ ይበል" ማለት ነው። እንዲህም ስለኾነ፦

ለዘቀደሳ ወአልዐላ እምኵሎን መዋዕል (ከዕለታት ኹሉ ለይቶ ከፍ ከፍ ላደረጋት ለበዓለ-ትንሣኤ) እንቋዕ አብጽሐክሙ--ዕሦ፣ ዕሠይ፣ ወሰው፣ ወሸን፣ ይበል፣ እንኳዕ (እንኳን) አደረሳችኹ!!! 


ድ.ክ.  = ድረ-ክታብ (P.S. = Post Script)

ምክታባችንን ለተወሰኑ ወራት ጦም በማሳደራችን ወዳጆቻችን ይቅርታ እንድታደርጉልን የሰሙነ-ትንሣኤን ዕለታት ስያሜ የያዘ ሰንጠረዥ እንደ እጅ መንሻ አባሪ አድርገንላችዃል።


Saturday, January 8, 2011

ምልማደ-ንባብ (የንባብ መልመጃ) -4

እንቋዕ አብጽሐነ አምላክነ
ለበዓለ-ወሊዶታ ለድንግል ኪያሁ ቤዛ-ኵልነ።
አምላካችን፦ ድንግል የኹላችን ቤዛ እሱን 
መውለዷ ለሚታሰብበት በዓል እንኳን አደረሰን።
የንባቡን ትምርት በድምፅ ለማስደገፍ አስፈላጊ ነገሮችን በማመቻቸት ላይ ነን። እስከዚያው ምክታባችን ጦም እንዳይሰነብት የዳዊትን ጣዕም ብንቀምስ ምን ይለናል። እነሆ እንደተለመደው የዚችን ክታብ ርእስ ኮርኩሙና መዝሙር ፩ን ተለማመዱ።