Wednesday, February 8, 2012

የመልአከ-ብረሃን አድማሱ ጀንበሬ መወድስ (ስለ ኤኩሜኒዝም)


[ባለፈው ክታባችን የጠቀስነው ቅኔ ትርጕም]

አባ አየለ የተባለ ካቶሊካዊ መነኵሴ፤ (በራሱ ምርምር አግኝቶት ሳይኾን ኢግናሲዮ ጕዪዲ የተባለ ጣሊያናዊ አዘጋጅቶ ያስቀመጠውን ገልብጦ) ለዶክትሬት ማዕርግ በበቃበት ጽሑፉ፤ ኢትዮጵያ ሃይማኖቷን ባታውቀው ነው እንጂ፤ ስለክርስቶስ “አካላዊ” ተዋሕዶ የምታምነው ነገር’ኮ ከሮማ ቤተ ክርስቲያን ትምርት አይለይም፤ ውስጡ ሲፈለፈል ያው “ኹለት ባሕርይ” የሚል ነው ለማለት ደፍሮ ነበር። ይኽንኑ ጽሑፉን በሮማ ካርዲናሎች መቅድም አሳጅቦ በጣሊያንኛ አዘጋጅቶ ባቀረበ ጊዜ፤ አቦ-አቦ እንጂ ሐይ የሚለው ባለማግኘቱ፤ ጥሩ ነገር የሠራ መስሎት ወዳማርኛ መልሶ ሊያሳትመው ችሏል። ደግነቱ ጊዜው ሊቃውንት ያልጠፉበት ዘመን ስለነበረ፤ አባ አየለ መጽሐፉን ከማን እንደቀዳው በሚገባ ባይደርሱበትም፤ የነገሩን ፍጹም ሐሰትነት ግን ከያቅጣጫው የተነሡ ሊቃውንት አስረድተዋል። ከነርሱም መካከል መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ያባ አየለን “ተነ-ሐሳብ” (የዐሳብ ብናኝ) በትንትኑን አውጥተው ድራሹን ባጠፉበት “መድሎተ-አሚን” (= የሃይማኖት ሚዛን) በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ 242 እና 243 ላይ የሚከተለውን አስፍረውልናል፦


“ስንኳንስ ይህን ያህል ደም መፋሰስ በነበረበት በዚያ ጊዜ፤ ዓለም ኹሉ ተስማምቶ ኹሉም እንደ ሃይመኖቱ በየወደደው ይኑር በሃይማኖት ምክንያት መከራከር መጨቃጨቅ ይቅር ብሎ በወሰነበት ባሁኑ ጊዜ እንኳን ቢሆን፤ በፍቅር የሃይማኖትን ነገር ለመረዳት ወደካቶሊካውያን ዘንድ የሚሔድ ኦርቶዶክሳዊ በኢትዮጵያውያን ውስጥ አይገኝም።
“የኸውም ሊታወቅ አሁን ባለንበት ባ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. በጎንደር ያሉ ካቶሊካውያን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በሚየከብሩበት ቀን የጎንደር ሕዝብና ካህናቱን ሊቃውንቱን ጠሩ...
“አርቆ ተመልካቾችና አስተዋዮች የኾኑ የጎንደር ሊቃውንትና ሕዝብ ግን ድሮ የፈሰሰውን ያባቶቻቸውን ደም ካለመዘንጋታቸውም በላይ ይህ ጥሪ ዛሬም የተሰበሰበውን ሕዝብ ፎቶግራፍ አንሥቶ የጎንደር ሕዝብ የካቶሊክን ሃይማኖት ተቀበለ ብሎ ወደሮማና ወደ ሌሎችም አገሮች ለመላክ፤ ኋላም ለሚነሡ ታሪክ ጸሐፊዎች አባ አየለ ኣፄ ካሌብ ካቶሊክ ነበሩ ፱ቱ ቅዱሳን ካቶሊካውያን ነበሩ እያሉ ለሚጽፉት መሠረተ ቢስ ወሬ ማዳበሪያ እንዲኾን የተዘጋጀ ዘዴ መኾኑን በመገንዘብ ተማምሎና ተገዛዝቶ ሳይሔደላቸው ቀረ።
“በዚህም ጊዜ የዚህ መጽሐፍ ባለቤት መ.ብ. አ. ለጎንደሮች የሚከተለውን መወድስ አበረከተ።”

እንትኰ በለሰ እመ-በላዕክሙ ወተጋባእክሙ ደርገ ኀበ-ሀለወ ገደላ
አንስርተ-ዲዮስቆሮስ ሊቅ ሊቃውንተ-ጎንደር ገሊላ
እሞትክሙ ሞተ ዘኢዩኤል ወእምየብሰት እስከ-ፍጻሜነ ዜናክሙ ሰግላ
በሊዐ-እክለ-ባዕድ እስመ ውእቱ
ዘበርእሰ-ነቢይ አብቈለ አፈ-አንበሳ-ሐቅል አሜከላ

ማዕዳኒ እንዘ-ንዉር በትፍዐ-ጽልዕ መሐላ
በዐልተ-በለስ እፎኑመ ጸውዐተክሙ ለበዐላ
ይገብሩኑ ኅቡረ በዓለ-ሐሤት ወተድላ
ደዋርህ (አርጋብ) ምስለ-አንቄ ወበግዕ ምስለ-ተኵላ

መልአከ ብርሃን አድማሱ በዚሁ መጽሐፋቸው “ያልቈጠሩትን ቅኔ እፈታለኹ ማለት ያላሳደጉትን ውሻ ጆሮ መቈንጠጥ ነው” ያሉትን አንብበናል። መልአከ ብርሃን ይኽንን ያሉበት ምክንያት አባ አየለ በመጽሐፉ የጠቀሳቸውን የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቅኔ ምስጢር ስንኳን ድርሱን ገመገሙን ሳያገኘው እንዲያው በድፍረት ለራሳቸው ለቅኔው ባለቤቶች “እንዲህ ማለታችሁ እንዲህ ማለታችሁ ነው” እያለ ሊዘላብድ መሞከሩ ገርሟቸው ነው። እኛ ግን ራሳቸው የቅኔው ባለቤት በሰጡን ቁልፍ አማካይነት የሐሳባቸውን መነሻ እና መድረሻ ስለተረዳን ፍቺውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል። እንዲህም ኾኖ ባፈታታችን የሙያ ወይም የምስጢር ዳኅፅ የታየው ሊቅ ሊያርመን ቢሻ ዕርማቱን በደስታ እንቀበላለን።

የሊቅ ዲዮስቆሮስ ንስሮች የገሊላ/የጎንደር ሊቃውንት ሆይ፦
ያችን [የባዕድ] በለስ ብትበሉ፤ ጥንብ ባለበትም በዚያ ባንድነት ብትሰበሰቡ ኖሮ
የኢዩኤልን ሞት በሞታችኹ፤ ዝናችኹ/በለስም እስክፍጻሜያችን በደረቀች ነበር።
በነቢዩ ራስ ላይ እሾኽ/የዱር አንበሳ አፍን ያበቀለበት (አንበሳ እንዲሰብረው ያደረገው)
የባዕድን እኽል መብላት ነውና።

ማዕዷም በመሐላ/ጠብ ትፋት የተነወረ ሲኾን
የበለስ ባለቤት እንደምን ለበዐሏ ጠራቻችኹ?
ዶሮች (ርግቦች) ከጭልፊቶች፣ በጎች ከተኩሎች ጋራ
ባንድነት የደስታና የተድላ በዓልን ያደርጋሉን?


ታሪክ


በመጽሐፈ-ነገሥት ተመዝግቦ እንደሚገኘው፤ አንድ ነቢየ-ጽድቅ (እውነተኛ ነቢይ) ከይሁዳ ወደቤቴል ደርሶ ሲመለስ እሰው ቤት ገብቶ እኽል እንዳይቀምስ ታዝዞ ሳለ፤ በባዕድ ነቢየ-ሐሰት (በማያውቀው ሐሰተኛ ነቢይ) ተታልሎ በዚሁ በሐሰተኛው ነቢይ ቤት ገብቶ በመብላቱ ምክንያት፤ የዱር አንበሳ በመንገድ አግኝቶ ገድሎታል። ይኸውም ድንገተኛ ነገር ሳይኾን መቅሠፍት መኾኑ ሊታወቅ አንበሳው ነቢዩን ቢሰብረውም ቅሉ ሬሳውን ሳይበላው፣ በቅሎውንማ ጭራሽ ሳይሰብረው ተገኝተዋል (1ነገ 13፡12-30)። የብሉይ ሊቃውንት እንደሚነግሩን የዚያ ነቢየ-ጽድቅ ስሙ አዶንያስ ወይም ኢዩ[ሄ]ኤል ይባላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጌታችን ባንድ ወቅት ከቅጠል ብቻ በቀር ፍሬ ያጣባትን የበለስ ዛፍ “እንግዲህ ወዲህ ለዘላለም ፍሬ አይገኝብሽ” ብሎ እንደረገማት፤ እሷም ወዲያውኑ ፈጥና እንደደረቀች በወንጌል እናነባለን (ማቴ 21፡19)።

ከዚህ በመነሣት የቅኔውን ምስጢር እንመልከት።

ምስጢር

እውነተኞቹ ኦርቶዶክሳውያን የጎንደር ሕዝብ እና ሊቃውንት ከሐሰተኞቹ ከካቶሊካውያን ማዕድ አንሳተፍም በማለታቸው ሊቁ መ.ብ. አድማሱ ጀንበሬ የተሰማቸውን የደስታ እና የአክብሮት ስሜት ለመግለጥ ባበረከቱት መወድስ፦ ጎንደሮች ድግሱን በልተው ቢኾን ኖሮ፤ እንደ ኢዩ[ሄ]ኤል ያለ አሟሟት ይሞቱ ነበር፤ ታሪካቸውም ጌታ ለዘላለም ደርቃ እንድትቀር እንደረገማት ፍሬ-ቢስ በለስ ምንምን የሚወሳ ፍሬ የሌለው ከንቱ ኾኖ ይቀር ነበር ብለዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ፤ ድሮ የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ጥርስ መስበሯ ጽሕም መንጨቷ፣ ተከታዮቹንም ማሳደዷ፤ ወደኢትዮጵያም ዘልቃ ገብታ በገዛ እጃችን (በሱስንዮስ) ስንትና-ስንት ሺሕ ነፍሳት ማስጠፋቷ ሳያንሳት፣ ትናንት በፋሺስቶቹ ዘመን የደብረ-ሊባኖስን መነኮሳትና አገልጋዮች ጨምሮ ስፍር ቊጥር የሌለው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማስጨረስ መሣሪያ ባርካ የላከች መኾኑን ታሪክ መዝግቦታል። ታዲያ እንዲህ ያለችው የበደል ባለቤት (በዐልተ-በለስ) ይኽንኑ በደሏን በምትችለው ክሳ በቀረው ይቅርታ ለምና በዕርቅ ሳታደርቅ፤ የሃይማኖቷንም ጥመት በትሕትና ሳታቃና፤ ኑ በዓሌን አክብሩልኝ ድግሴን ብሉልኝ ብላ እንደምን ልትጋብዝ እንደቻለች ሊቁ በወቀሳ አንክሮ ጠይቀዋል።

በመጨረሻም ረ ለመኾኑ ርግብ እና ጭልፊት፣ በግ እና ተኵላ መች አንድ ላይ ይውላል? በማለት ደም በዕርቅ ሳይደርቅ፣ ሃይማኖትም በትሕትና ሳይቀና፣ ኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ በደስታ እና በተድላ እንደማይገናኝ አስተምረውናል።

ዘቦ ዕዝን ሰሚአ ለይስማእ!

2 comments: