Thursday, February 2, 2012

ግእዝ እና ንባበ-መለኮት፦ ለእስ-በስ ውይይት (Geez and Theology: A Colloquy)[ይችን የምክታብ ድረ-ገጽ (“ግእዝ በመሥመር ላይ”ን) ከሠየምናት ዓመት ኾነን። ሥራውን እንዳጀማመራችን ሳንቀጥል እንደገና ወደዃላ ተመልሰን እስካኹን በዝግጅት እየባተልን አለን። ይኹን እንጂ የግእዝ መፍቀርያን የቱን ያኽል እንደኾኑ፤ ፌስቡክ በተባለው የገጽ መጣፍ ላይ ባለን አድራሻ በነጻ መወዳጀት የሚቻለውን የጓደኞች ቊጥር (5000) ገና ዓመት ሳይሞላን ገደቡን ማለፋችን አስደምሞናል። እሶ፣ እሰይ፣ ግእዝ አኹንም ዘመደ-ብዙ ነው ለካ! እንዲህ ነውና እኛም ትምርቱን አጠናክረን እንቀጥላለን። ዛሬ ግን፤ ከቋንቋው ጋር ትይይዝ ባለው አንድ ሃይማኖታዊ ጕዳይ ላይ እንተኩራለን።]


ግእዝ እና ንባበ-መለኮት፦ ለእስ-በስ ውይይት (Geez and Theology: A Colloquy)

ይች ክታብ ሰላማዊ ንግግርን ብቻ ሳይኾን (በእሰጥ-አገባም ይኹን በሌላ መንገድ) ጭቅጭቅን፣ ግጥሚያን እና ፍጥጫን ጭምር ሊያካትት ወደሚችለው “የእስ-ከሌላ ውይይት” (ዲያ-ሎግ) ዘው ብሎ ከመግባት በፊት፤ ለእንዲህ ያለው ውይይት መነሻ በሚኾን ጕዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ባለን ወገኖች መካከል “የስ-በስ ውይይት” (ኮሎኵዊ) ቢደረግ እንደሚሻል በማመን የተዘጋጀች ናት። በግልጥ ለማስቀመጥ፤ ስለ“ተዋሕዶ መለኮት ወትስብእት” አንድ ዐይነት እምነት ያለን ወገኖች፤ ከእኛ የተለየ እምነት ካላቸው ከሌሎች ጋራ ውይይት ከማድረጋችን በፊት፤ ስለጉዳዩም ኾነ ስለውይይቱ አካኼድ ያለንን አቋም ለራሳችን በውል ለመረዳት እና ለሌሎቹም አጠናክሮ ለመግለጥ አስቀድመን እስበሳችን ብንወያይ መልካም ስለኾነ፤ ወደዚሁ ዓላማ ለማምራት እንዲበጅ የሚከተለውን አቅርበናል።

ስለ“ምዕራባውያን” አቋም ጠቅለል ባለ መልኩ

ምዕራባውያን ባህላቸው የቆመው በኹለት ዐበይት አብነቶች ላይ ተመሥርቶ እንደኾነ ያምናሉ። ሃይማኖታቸውም እንዲሁ (ለነገሩ በነሱ አስተያየት ሃይማኖት’ኮ የባህል “ንኡስ ስብስብ” ነው)። እሊህም ኹለት አብነቶች በየመናገሻ ከተሞቻቸው ስም ሲጠሩ፦ “ኢየሩሳሌም” እና “አቴና” ይባላሉ። ኢየሩሳሌም፦ የመዐልቱን (የንጋቱን) መምጣት አስቀድማ እንደምታበስረው የማለዳ ዎፍ በመንፈሰ-እግዚአብሔር ተቃኝቶ የሚኾነውን ኹሉ ከመኾኑ አስቀድሞ የመናገርን፤ ያንኑም “ይቤ እግዚአብሔር” እያሉ በእግዚአብሔር ስም የማስተማርን ትንቢታዊ ሥራት ስትወክል፤ አቴና ደግሞ፦ መዐልቱ (ቀኑ) ካለፈ በዃላ ተነሥታ በጨለማ ከወዲያ ወዲህ እንደምትባክነው የሌት ዎፍ የኾነው ኹሉ ከኾነ ወዲያ ምንነቱን ለመረዳት በዕሩቅ አእምሮ-ጠባይዕ (with mere/pure reason) የማውጣት የማውረድን፣ የመመራመርን ፍልስፍናዊ ፈሊጥ ታመለክታለች።

ታዲያ እሊኽን ኹለት አብነቶች አጣጥሞ የመጓዙ ኺደት ለምዕራባውያኑ ቀላል አልኾነላቸውም። ከክርስትና ወዲህ ያለውን ጊዜ ወስደን፤ ከዚያውም ላይ ገና በዘመነ-ሐዋርያት የተከሠተውንና በአሥራው መጻሕፍት ተመዝግቦ የሚገኘውን ትተን፤ በዘመነ-ሊቃውንት የነበረውን ኹናቴ ብቻ ብናስታወስ፤ አኹን ድረስ ዘልቀው ለመጡ የተለያዩ ዝንባሌዎች መነሻቸው ምን እንደነበር ወለል አድርጎ ያሳየናል።

በአንድ በኩል፦ ሀብተ-ጥምቀትን ከተቀበሉም በዃላ በአሕዛባዊ ማንነታቸው ጸንተው ለመዝለቅ የዳዳቸው ምሁራን ቅዱሳት መጻሕፍትን በጽርእ ፍልስፍና መሠረት ለማተት ሲሹ፤ በሌላ በኩል፦ ለቅዱሳት መጻሕፍት ተጨልጠው ተገርኝተው የተገዙ ሊቃውንት “ለመኾኑ አቴናን ከኢየሩሳሌም ማን አገናኛት?” በማለት የጽርእን ፍልስፍና ባህል ወዲያ በሉልን ብለው በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት ብቻ ለመጓዝ ወስነው ነበር።

በእሊህ ኹለት ዝንባሌዎች የሚታየውን የጽንፈኝነት አደጋ የተገነዘቡ ምሁራን፤ በተለይም በአንጾኪያ እና በእስክንድርያ ዃላም በቊስጥንጥንያ የተነሡ ሊቃውንት ደግሞ፤ የጽርኡን ፍልስፍና ከቅዱሳት መጻሕፍት በማጣጣሙ ኺደት የክርስትና ሃይማኖት ምሰሶዎች ለኾኑት ምስጢራት ልክ እና መልክ ሊሰጧቸው “ውሳኔ” ሊያበጁላቸው ሞክረዋል--በመንፈስ ቅዱስ መሪነት። “ዶግማ” ማለት ቅሉ “ውሳኔ-ሃይማኖት” ማለት ነው፦ አዕማደ-ምስጢርን የሚወስን።

ሮም ግን አንድ ሳትሠራ ከላይ በተጠቀሱት ትምርት ቤቶች ተቦክቶ የተጋገረውን እየሰለቀጠች እኔ ነኝ ወይዘሮ ለማለት ፈለገች። ስለዚህ--በማታውቀው ጕዳይ ማለት ይቻላል--ዳኝነት እሰጣለኹ ብላ፤ ያውም በስማ በለው፤ ጳጳሳቷን በኬልቄዶን አንጫጫች። በዚህም ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ እንደሚያስተምረን በኢሳይያስ 23፡1 “ለየዐውይዋ አሕማረ ኬልቄዶን እስመ-ተኀጕላ” (ተሰብረዋልና የኬልቄዶን መርከቦች ያልቅሱ!) የተባለው ትንቢት ተፈጽሞባታል።

“ችግሩ’ኮ የቋንቋ ብቻ ነው”፦ ጥንቱንስ የምን ችግር ኖሯል?

“ኤኩሜኒዝም” ወይም “የአብያተ-ክርስቲያን አንድነት ፍለጋ” በሚል ንስሺ/መነሾ ከወዲያ ወዲህ የሚሉ እንቅስቃሴዎችን ስንሰማ እና ስናይ አንድ ምእት ዓመት አለፈን። ነገሩ እየጠነከረ ኼዶ ዛሬ እኛውም ቅሉ ራሳችን ከወዲህ ወዲያ ልንል እየተንደረደርን ነው። ረ እየተፈነጠርን እንጂ። ላይ ላዩን ሲታይ፤ ነገሩ መለያየትን የመጥላት አንድነትን የመፈለግ አዝማሚያ ያለው ይመስላል። ወስጥ ውስጡንሳ? ወስጡንማ ለቄስ። ግን እንደጨዋም ቢኾን የሰማነውን አንድ ጉዳይ እናንሣ። ቋንቋ።

ጥንት ያላግባብ “ሞኖፊሳይት” ሲባሉ በኖሩት፣አኹንም ያላግባብ “ኦሪየንታል” በሚባሉት “የርትዕት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” አባላት እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ሲካኼዱ ከቆዩ ውይይቶች፤ ለሮም እጅግ የረባ ሙድሙድ የተደረገው በ“ቪየና ኮንሰልቴሽን” ነው። “የቋንቋ ችግር” የተባለው ዋና ማደናገሪያ ሥራውን የሠራበት ሙድሙድ። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ባጭሩ፦

የሮም የሠርግ ድግስ በቪየና፦ “ወትቤ ሮም” (የቪየናው ኮንሰልቴሽን ጠንሳሽ፣ አዘጋጅ፣ አስተናባሪ... ውሎ አበል ከፋይ... ጕዳዩን ጐዳይ፣ ጥያቄውን ተካይ... ሮምም አለች)፦
“ኦርየንታሎች” ሆይ፦ ችግሩ’ኮ በኬልቄዶን የተወሰነው ረቂቅ እና ጥልቅ ትምህርተ-ሃይማኖት ቋንቋው ስላልገባችኹ ነው እንጂ፤ ከእሱ የራቀ ወይም የተለየ እምነት የላችኹም። (“ቋንቋው ስላልገባችኹ” ማለትም “በምስጢረ-ሥጋዌ አገላለጽ ቁልፍ የኾኑት የጽርእ ቃላት የቋጠሯቸውን በመሠረታቸው ጽርኣዊ፣ ፍልስፍናዊ የኾኑትን ፅንሰ-ሐሳቦች ያለመረዳት ችግር ስላለባችኹ ነው” ማለት ነው።) ስለዚህ እንደኛ ለመርቀቅ እና ለመጥለቅ ተስኗችኹ “ኹለት ባሕርይ” ማለት ከብዶ ከታያችኹ፤ የኬልቄዶኑን ትምርት እስከዛሬ በያዛችኹት መንገድ ሳይኾን አኹን እንደዐዲስ መረዳት በምትችሉት መጠን፣ እንዳቅማችኹ፣ እንደሚመቻችኹ ግለጡትና እንስማማ... ከበር ቻቻ።
ያብዛኞቹ የኦርየንታል ተወካዮች የመልስ ድግስ፦ (ግብፅን ጨምሮ፤ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦በቅድሚያ ስለጋበዛችኹን... ለዚህ ወይም ለዚያ ፕሮጀክት ድጋፍ ስላደረጋችኹልን... እያመሰገን)፦
እውነታችኹ ነው። ለካ እንዲያ ኖሯል! አኻ፤ አባቶቻችን ባይደርሱበት ነው እንጂ የኬልቄዶን ውሳኔ ቀና ኖሯል፣ እንዴት ተሸፍኖባቸው ነበር ባካችኹ!... አኹን ግን እሺ፤ ነገሩ ለእኛ ለልጆቻቸው(?) ተገልጦልናልና እንዳላችኹት ይኹን... ለጊዜው እንዲህ ብለን ተስማምተናል... ወደፊት ደግሞ በቸርነታችኹ በምትሰጡን ስኮላርሺፕ ጽርኡን ከነፍልስፍናው ተምረን ዐይኖቻችን ሲበሩልን፣ ነገሩ በደንብ ሲገባን ሙሉ በሙሉ የናንተን አገላለጽ  እንከተላለን። ለካ ቋንቋ ኖሯል ችግሩ!... ከበር ቻቻ፤ እንደገና።
የፊርማ  ቅልቅል (ባስታ! = አለቀ፤ ደቀቀ።)

ባገራችንም፦ ዐይናሞቹ ሊቃውንት “አንደኛ ቀጥተኛ፣ ቅን፣ እንከን የሌለው ቋንቋ” እንደኾነ የሚናገሩለትን ግእዝን (አላዋቂን ለማጭበርበር ያኽል እንዲያው በጥራዝ-ነጠቅ ኪጠቀሙበት በቀር፤) ስንኳን ውሳጣዊ ባሕርዩን መረዳት፤ አፍኣዊ ገላውን አይተው ተነሹን ከወዳቂው፣ ተነባቢውን ከባዕዱ፣ የሚጠብቀውን ከሚላላው፣ በፍቅደት የሚነበበውን በውሕጠት ከሚነበበው፣ አጎበሩ/ትርኣሱ የሚነሣበትን ከሚወድቅበት ጠባዩ፣ መለየት የማይችሉቱን ትታችዃቸው፤ ቅኔ ከነአገባቡ ጠንቅቀው ከሚያውቁት ትርጓሜ-መጻሕፍትንም አሳምረው ከሚያኼዱት መካከል ሳይቀር ብዙዎች “ችግሩ በቀላሉ የሚፈታ ተራ የቋንቋ ጣጣ ነው” በሚለው ሸፍጥ ሲታለሉ ይታያሉ። 

የቅዱሳት መጻሕፍት ቋንቋ፣ የክርስትና ቋንቋ

ቅዱሳት መጻሕፍት የተደረሱት በመንፈስቅዱስ ነው። እንዲህም ስለኾነ፤ የምስጢራቸው ምንጭ ሰማያዊ፣ መንፈሳዊ ነው። “ወተናገሮ እግዚአብሔር ለአብርሃም በልሳነ-ፍጥረቱ” እንዲል፤ ከሰማይ የመነጨው ምስጢር በምድራዊ ቋንቋ ተገልጧልና ሰማያዊው ምስጢር ቀድሞ ለተገለጠበት ምድራዊ ቋንቋ ትኩረት መስጠት ያሻል ከተባለ ደግሞ፤ ያ ቀዳሚ የአብርሃም ቋንቋ ዕብራይስጥ እንጂ ጽርእ (ግሪክኛ) አይደለም። በርግጥ ከአሕዛብ ወገን ክርስቶስን አምነው የተቀበሉት አብዛኞቹ በጽርእ ቋንቋ እና ባህል ተጽእኖ ሥር ስለነበሩ፤ ሐዋርያት ወንጌልን ሲጽፉም ኾነ ላንዱም ላንዱ አካባቢ መልእክት ሲልኩ የተጠቀሙበት ቋንቋ ጽርእ ነበር። እንዲህ ስለኾነ ግን ጽርእን የሐዲስ ኪዳን መሠረታዊ ቋንቋ አያደርገውም። ምክንያቱም ሐዋርያት ዕብራውያን ናቸው። ጌታም ያስተማራቸው በዕብራይስጥ (በአራማይክ) ነው። የየዐይነተኛ ዕሳቤዎቹ ጸዋትወ-ምስጢር (category = “ምስትውዳይ”) የተተከለው ለነቢያትም፣ ለጌታም፣ ለነሱም የጋራ መግባቢያ በነበረው ቋንቋ ሕግ እና ሥራት (grammar, idiom) ነው። አግባቡም (its logic) በሊሁ ልማድ የተወሰነ ነው። ስለዚህ በቅጥነተ-ልብ ካስተዋልነው ሐዋርያት ወንጌልንም ኾነ መልእክቶቻቸውን ሲጽፉ ገና በማዕርገ-ኅሊ ሳለ (at the level of thought) ከዕብራይስጥ ወደጽርእ መልሰው ነውና፤ እነሆ የጽርኡ ወንጌልም ኾነ መልእክት በዕብራይስጥ ታስቦ የተነገረው ነገር ቅጂ ኾኖ እናገኘዋለን። ቅጂነቱ ግን የመጀመሪያ እና በገዛ ደራስያኑ--ከጽሑፍ ወደ ጽሑፍ ያይደለ ካፍ ወደ መጣፍ--የተከናወነ እንደመኾኑ መጠን፤ የተከበረ ቦታ ሊሰጠው ይገባ ይኾናል። ከዚህ አልፎ ግን ጽርእን እንደልዩ እና ብቸኛ የክርስትና ቋንቋ ማየት--ይልቁንም የሐዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችን በጽርእ ፍልስፍና (እ)ሥር እንደነበሩ መገመት--ግልብነት ነው።

ለምሳሌ ያኽል በዮሐንስ ወንጌል “ቀዳሚሁ ቃል” ያለውን ለዕብራውያን አስተሳሰብ ባዕድ የነበረ የጽርእ ፍልስፍና አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚሞከረው ነገር ፉርሽ ኾኖ እናገኘዋለን። የዚህን ኀይለ-ቃል ትርጕም አበው እንደሚፈትቱልን ኦሪት “በቀዳሚ ገብረ ሰማየ ወምድረ” (“በቀዳማዊ ቃሉ...”) ያለችውን አስታውሶ፤ በዚያው መሠረት ላይ “ቀዳሚሁ ቃል” (ያ ቃል-- በኦሪት ዓለምን እንደፈጠረ የተነገረለት ቀዳማዊ ቃል) ሥጋ ለበሰ በማለት በጊዜው ጊዜ የፈጸመውን ቸርነት ከሚነግረን በቀር፤ ከጽርእ ፍልስፍና ለቅዱሳት መጻሕፍት ስሯጽ ኾኖ የገባ “የሎጎስ ታኦርያ” አይደለም። በዚህም የመሰለውን ኹሉ ልብ ይሏል።

ይህ እንዲህ ነው፤ ይኹን እንጂ አሕዛብ እውነተኛውን ፈጣሪያቸውን አምነው ሕይወታቸውን በክርስትና መንገድ ለመቀጠል ቅዱሳት መጻሕፍትን መመሪያቸው ሲያደርጉ፤ በዕብራይስጥ የተገለጠውን በጽርእም የተጣፈውን ሰማያዊ፣ መንፈሳዊ ምስጢር ለመረዳት እና ለማብራራት፤ የጽርኡን ቋንቋ እና ፍልስፍና በመሣሪያነት በስፋት ተጠቅመውበት እንደነበር አይካድም። የቋንቋውም ኾነ የፍልስፍናው መሣሪያነት ግን ሕፀፅ ያለበት ነው። (ሕፀፁን በምስክር አስደግፈን በሌላ ጊዜ እናሳያለን።)

ኢትዮጵያ በበኩሏ ከእስራኤል ጋር እንደ እስራኤል ብሉያትን ይዛ የቆየች እና ከጽርእ ቋንቋ እና ባህል ቀጥተኛ ተጽእኖ ውጭ የነበረች በመኾኗ ላይ፤ ሐዲሳትን ከብሉያት አስማምታ ስትቀበል መጻሕፍቱን እንደጥንቱ ለሰማያዊው፣ ለመንፈሳዊው ምስጢር መግለጫነት ምቹ ወደኾነው ወደባሕርያዊ ልሳኗ ወደግእዝ መልሳ ነው። ያውም በወቅቱ። እንደ ዐይናማው ሊቅ እንደ አለቃ አያሌው አነጋገር፦ “ዓለም ልቡ ሳይሸረሙጥ!” አለቃ አያሌው ይኽንን ሲሉ የሰማነው፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደገና ከዕብራይስጥ እና ከጽርእ አስማምቶ እንዲተረጕም በተሠየመ ኮሚቴ ውስጥ ሲሠሩ፤ የጽርኡን እናት ለመወሰን በነበረው ጥረት ከጽርኣውያኑ ወገን የተመደቡት ሊቃውንት “የኸ ነው ትክክሉ፣ የለም ያኛው ነው” በመባባል በትክክለኛው አብነት (version) ሊስማሙ ባለመቻላቸው ሥራው መቋረጡን ሲያስታውሱ ነበር። እንደርሳቸው አገላለጽ የአብነት ልዩነቱ እየተስፋፋ የኼደው ዓለም ልቡ በመሸርሞጡ ምክንያት ነው። 

ከዚህ አያይዘን ግእዝ ከዕብራይስጥ ጋር እንዴት ያለ ዝምድና እንዳለው ብናትት መልካም በኾነ ነበር፤ ነገር ግን (እንዲያው በከንቱም ቢኾን) ከወዲህ ወዲያ ለምንዋትትበት የግል ግዳጅ ጊዜ እያጠረን ስለተቸገርን አኹን አልፈነዋል። ብንኖር፣ እግዜርም ቢፈቅድልን በሌላ ጊዜ ተመልሰን እንተነትነዋለን...

በምስጢረ-ሥጋዌ በኩል ላለው ክርክር ዋናው ቊልፍ፦ የቅዱስ ቄርሎስ አገላለጽ

በጉባኤ-ኒቅያ የሃይማኖት ርትዐት (የሃይማኖት ቀናነት/ቀጥተኛነት) መለኪያው አካላዊ ቃል በአብ ዕሪና እንዳለ ("ዘዕሩይ ምስለ-አብ በመለኮቱ" መኾኑን) ማመን እና ማስተማር መኾኑ ስለተገለጠ፤ ይህንኑ የተቀበሉ ሊቃውንት ርቱዐነ-ሃይማኖት ሲባሉ፤ ከዚህ የወጣ ነገር የሚያምኑ እና የሚያስተምሩቱ ግን መናፍቃን ተብለው ተለይተዋል። ዃላ ደግሞ በጉባኤ-ኤፌሶን አካላዊ ቃል ሰው ሲኾን፤ መለኮት ከትስብእት በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መኾናቸው ተገልጦ፤ ይህንኑ የሚያምኑና የሚያስተምሩ ሊቃውንት የተዋሕዶ አበጋዞች ኾነው ሲከበሩ፤ ከዚህ ወጥተው የምንታዌ ዐሳብን ሊያራምዱ የፈለጉቱ ግን መናፍቃን ተብለው ተለይተዋል። በኤፌሶን ለነበሩት ሊቃውንት ዋና ፊታውራሪያቸውም ቅዱስ ቄርሎስ ነው። ቅዱስ ቄርሎስ ከመናፍቃኑ ጋራ የተከራከረበት እና ለምእመናን ያስተማረው ነገር ጭማቂው “አሐዱ ባሕርይ ዘእግዚአብሔር ቃል ሥግው” የሚል ነው።

ይኽንን ፍሬ-ነገር በስፋት እና በጥልቀት ያብራራባቸው የቅዱስ ቄርሎስ ድርሰቶች ዛሬ በተሟላ መልኩ የሚገኙት፣ በጽርእም፣ በሮማይስጥም/በላቲንም በቅብጥም፣ በሱርስትም፣ በዐረብም አይደለም። በግእዝ ብቻ ነው። እንዲህም በመኾኑ፤ በብጥስጣሽ መልኩ ብቻ የሚገኘውን የጽርኡን እናት (ኦሪጂናሌ) በኺደት ለማሟላት ከግእዙ ሌላ ምንም ዐይነት ታማኝ ምንጭ ስላልተገኘ፤ ቫይሸር የተባለ ጀርመናዊ ምሁር የግእዙን ቄርሎስ በሰፊ ጊዜ እና ድካም ለጊዜው ወደጀርመንኛ መልሶ በ5 ቅጽ አሳትሞታል። ይህ የሚያሳየን፤ ግብፅን ጨምሮ ሌላው ዓለም በቀጠፋ ጥቅስ ሲማቅቅ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሙሉውን ቄርሎስ ለአንድ ሺሕ ተእኩል ዓመታት (1500) ያኽል እያነበበች ስትተረጕም፣ እያራቀቀች ስታስተምር እነሆ እዚህ ደርሳለች። (ምናልባት ዛሬ ወንበሩ ሊታጠፍ ተቃርቦ እንደኾነ፤ ማዘን እና መጸለይ ልብ ያለው ምእመን ተግባር ነው።)

ታዲያሳ፦ የእኛዪቱም የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “ባሕርይ” እና “ህላዌ”፣ “አካል” እና “ግጻዌ/ገጽ”፣ እሊህንም የመሳሰሉትን ጸዋትወ-ምስጢራት (ዕሳቤዎች/ፅንሰ-ሐሳቦች) ጠንቅቃ ያልተረዳች ይመስል፤ “ለካ ቸግሩ የቋንቋ ኖሯል፤ አኹን ገና ገባኝ” ብላ ከደቂቀ-ልዮን፣ ከአሕማረ-ኬልቄዶን ጋራ አብራ መንጎድ ይገባታልን?

የሸፍጥ ለውጥ፦ ከ“ሞኖፊሳይት” ወደ “ኦርየንታል”

ሊቃውንት የወንጌሉን ቃል ተከትለው በግልጥ ቋንቋ “በኵሉ ግብሩ ወልድ ዋሕድ” በማለት ፍጹም አንድነቱን የሚመሰክሩለትን ሥግው ቃል (ሥጋ የለበሰ ቃል)፣ አምላክ ወሰብእ (ሰው የኾነ አምላክ) ክርስቶስን፤ ሮማውያኑ እንዲያው በጕሥዐተ-ኅሊና (በትቢት የተደፈነ ልባቸው በሚያገሳው ብስና የተሞላ አፋቸው እንዳመጣላቸው) ኾልተው (ኹለት አድርገው) ሲያበቁ፤ የቅዱስ ዲዮስቆሮስን የቀናች ሃይማኖት የጎደፈች ለማስመሰል፤ ተከታዮቹን “ሞኖፊሳይት” እያሉ ሲጠሩ መኖራቸው የማይካድ ነው። ነገር ግን ቅዱስ ዲዮስቆሮስም ኾነ ተከታዮቹ በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት ላይ የጸናውን እና ከርቱዐነ-ሃይማኖት አባቶቹ እና ወንድሞቹ አገላለጽ የተስማማ መኾኑ በጉባኤ-ኤፌሶን የተረጋገጠለትን የቅዱስ ቄርሎስን ትምርት ጠብቀው ከመገኘታቸው በቀር፤ በትምርት ገበታ አንድ ቀን ታይቶ የማይታወቅ አውጣኪ የተባለ የመኳንንት እና የወይዛዝርት አጫዋች መነኩሴ መሠረተው ከሚባለው የ“ሞኖፊሳይት” አስተሳሰብ አንዳችም ንክኪ እንዳልነበራቸው የሮማውያኑ ቅሉ ኾዳቸው የሚያውቀው ነገር ነበር። ነገር ግን ቅዱስ ዲዮስቆሮስንም ኾነ ተከታዮቹን ማንቋሸሻ ሌላ ምክንያት ቢያጡ፤ በምስጢር ረገድ እዚህ ግባ በማይባለው በአውጣኪ ስም ተፈጠረ ያሉትን ኑፋቄ የዲዮስቆሮስ እና የተከታዮቹ ትምርት እንደኾነ አድርገው በማስመሰል ያለስማችን ስም ለጥፈውብን ኖረዋል።

ዛሬ ካንገት በላይ በጀመሩት ዝምድና “ሞኖፊሳይት” ብሎ ያለስማችን መጥራቱን አግባብ እንዳልነበረ በማመን ሰርዘነዋል ብለው ሲተውት፤ በዚያው አንጻር እምነታችንን በትክክል በሚያንጸባርቀው የቅዱስ ቄርሎስ ቃል መሠረት “ሚያፊሳይት” (ውሉደ-ተዋሕዶ) ሊሉን በቻሉ እና በተገባ ነበር። እነርሱ ግን ያንን መንገድ አልተከተሉም። ከሃይማኖታዊ መታወቂያ ዘለው ወደመልክአ-ምድራዊ አጠራር ገቡና “ኦሪየንታል” አሉን እንጂ። ለመኾኑ ኢትዮጵያ “ኦርይንት” ናት? ግብፅስ ብትኾን? ሌሎቹስ?... በዚህ ዐውደ-ነገር (በዚህ ነገር ትይይዝ) “ኦርየንት” ማለት’ኮ ሮም በኹለት ተከፍላ ምዕራቡ “ኦክሲደንት” ሲባል ቀሪው ምሥራቃዊ ክፍሏ ይጠራበት የነበረ ቃል ነው! (ኦርየንት + ኦክሲደንት = ሮም) ለመኾኑ እኛ መቼ የሮማ አካል ነብረን እናውቀለን? ወደፊትስ? ምናልባት ይዳዳን ይኾን እንዴ? (የሳት ልጅ ዐመዶች!)

ወዳጆች፦ እውነት እና ዕውቀት ወደቊሳዊ መረጃነት እና የመረጃ ይዞታ ዘቅጠው ባለበት (mere information በኾኑበት)፣ በገንዘብ በሚሸጡ እና በሚገዙበት “በ21ኛው ክ/ዘመን”፤ በኼድንበት ኹሉ፤ በዚህም በዚያም ብሎ ከርሡን የሚያገለግል እንጂ ጽድቅን የሚያስባት ለማግኘት ጭንቅ ኾኗል። “ለጽድቅ ኢንዜከራ ወኢትዜከረነ ጽድቅ!” አሉ፤ ባለቅኔው። “እውነትን አናስባትም እሷም አታስበንም!” ማለት ነው። ስለዚህ፦ ጠንቀቅ ማለት አይሻልም?!

በሉ ለጊዜው በዐይናማው ሊቅ፣ በቅኔ ፈጣሪው በመልአከ-ብረሃን አድማሱ ጀምበሬ መወድስ እንሰነባበት፦

እንትኰ በለሰ እመ-በላዕክሙ ወተጋባእክሙ ደርገ ኀበ-ሀለወ ገደላ
አንስርተ-ዲዮስቆሮስ ሊቅ ሊቃውንተ-ጎንደር ገሊላ
እሞትክሙ ሞተ ዘኢዩኤል ወእምየብሰት እስከ-ፍጻሜነ ዜናክሙ ሰግላ
በሊዐ-እክለ-ባዕድ እስመ ውእቱ
ዘበርእሰ-ነቢይ አብቈለ አፈ-አንበሳ-ሐቅል አሜከላ
ማዕዳኒ እንዘ-ነውር በትፍዐ-ጽልዕ መሐላ
በዐልተ-በለስ እፎኑመ ጸውዐተክሙ ለበዐላ
ይገብሩኑ ኅቡረ በዐለ-ሐሤት ወተድላ
ደዋርህ (አርጋብ) ምስለ-አንቄ ወበግዕ ምስለ-ተኵላ

(እምየዋ! እምየ አድማሱ ጀምበሬ። ምነው በዕድሜ ደርሰን ዐይንዎን አይተን ድምፅዎን ሰምተን በነበር። ዛሬማ ቸልታችንን ዕድሜ ይንሳው እና ኹሉን ነገር ችላ ብለን ለነአባ እንቶኔ ስለተውነው፤ እንደናንተ ያሉቱን ሊቃውንት አሟጥጠን ጨርሰን፤ ቤተክሲያናችን ቀኝ እና ግራቸውን በማይለዩ ገላግልት እየተወከለች የነውር ማዕድ ትፈተፍት ይዛለች። ይኸ ቀን ያልፍ ይኾን?!)
ፍ.ታ.ፈ.

2 comments:

  1. ማለፊያ ነው ፡፡ ይበል ብለናል

    ReplyDelete
  2. heart touching!! wanza belelebet min yimeretal endilu!!

    ReplyDelete