Friday, March 9, 2012

ስለኹለቱ ሥርዐታተ-ተምህርት

መወድስ

(ፍሬ መወድስ፦ “ፍታሕ ሊተ እግዚኦ ወተበቀ፟ል በቀልየ!”)

በውስተ᎘ ቤታ ለእም ኢትዮጵያ
ጉቡኣነ ደርገ እንዘ᎘ ይዛውዑ ዛውዐ
ከንቶ ነገረ እለተናሥኡ ኵርናዐ
ጠባይዐ᎘ ቀደምት ኣሐደ[1] ወትምህርተ᎘ ደኀርት ካልዐ
መኑመ፟ እንበለ᎘ ዘሀሎ ያስተሳልም ስምዐ
ለለአሐዱ እምዘአምዕዐ፤
ብሂለ᎘ ጠዋይ ጠዋየ ወብሂለ᎘ ርቱዕ ርቱዐ

(ለዓለም፦ “ለዓለም ወለዓለመ᎘ ዓለም!”)

መምህረ᎘ ሕግሂ ድኅርና ግዕዘ᎘ ካልዑ ዘጠግዐ
ቅድምና ባሕርየ᎘ ርእሱ ፍጹመ በዘአጽንዐ
እምውሉደ᎘ ምዕራብ አብያጺሁ እለልማዶሙ ፀዕዐ
ላሕየ᎘ ጉባኤሁ ይሤኒ ዳዊት ከመአይድዐ

ትርጕም


(የፍሬ መወድሱ)

በእናት/ኢትዮጵያ ቤት ውስጥ
ባንድነት/በደርግ ተሰብስበው ጨወትን ሲጨዋወቱ
በማይረባ ነገር ክንድ የተነሣሡ
አንደኛውን/የቀድሞዎችን ጠባይ (the Classical) እና ሌላኛውን/የኋላኞችን ትምርት (the Modern)
ከነበረ (ከ“ዘሀሎ”/ከእግዜር) በቀር (እንዲያው ለመኾኑ!) ማን መስክሮ ያስታርቃል?
አንዱንም አንዱን ካስቆጣው ነገር ጠማማውን ጠማማ፣ የቀናውንም የቀና በማለት (ማን መስክሮ ያስታርቃል?)

(የለዓለሙ)

ከደኃራዊነት (Temporality)/ከሌላ ልማድ የተጠጋ የሕግ መምህርም 
ቀዳማዊነትን (Eternity)/የራሱን ባሕሪ ፈጽሞ ባጸና ገንዘብ
ትምርታቸው ከሚያብለጨልጨው ከባልንጀሮቹ/ከምዕራብ ልጆች ይልቅ 
መልኩ/ጉባኤው ያምራል፤ ዳዊት እንደተናገረ።

ምስጢር

ዘመናዊ ትምርት ወዳገራችን ከገባ ጊዜ ጀምሮ፤ ኹለቱ ሥርዐታተ-ትመህርት (ጥንታዊው ኢትዮጵያዊው እና ዘመናዊው ምዕራባዊው ማለታችን ነው) ተጣጥመው የሚያውቁት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው (ይኸውም በእንጦጦ ራጉኤል ተማሮቸ በእነ ብላቴን ጌታ ሩይ ወልደ-ሥላሴ ጊዜ)። በተለይም በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ-ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት መገባደጃ ላይ “ሥር-ነቀል” ለውጥ በምር ስለተፈለገ፤ ለውጡ ተፈጽሞ ደርግ ሲነግሥ መጤው ዘመናዊ ትምርት ነባሩን ጥንታዊ ሥራት ሙሉ በሙሉ ለማስለቀቅ በቅቷል። ውጤቱ ግን ያየነው እና እያየነው ያለው ነው። በመኾኑም፤ የራሱ የዘመናዊው ሥራት ውጤት የኾኑ ምሁራን ሳይቀሩ ስሕተቱን አስተውለው ወደጥንታዊው አገራዊ ሥራት የምንመለስበትን መንገድ በመፈለግ ላይ ናቸው። (ለአብነት እነ ፕሮፌሶር መሳይ ከበደ፣ ተከሥተ ነጋሽ፣ ማእምረ መና-ሰማይ እና ጳውሎስ ሚልክያስን መጥቀስ ይቻላል። ፕሮፌሶር ጌታቸውን የመሳሰሉት ግን ጥንቱንም መሠረታቸው አገራዊው ሥራት ነው።)

ዳዊት በመዝሙሩ “የሕግ መምህር” ያለው አካላዊ ቃል ወልድ በደኀሪ ዘመን (in time) ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ሲኾንና ዘመን ሲቆጠርለት ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ባንድነት ከነበረው ቅድምና (eternity) ሳይናወጥ ነው። “ወእምድኅረ ተሠገወ ነበረ ክመ ቃለ።” (ሥጋን ከተዋሐደም ወዲያ በቀዳማዊ ቃልነቱ ጸንቶ ኖረ) እንዲል ሊቁ።ስለኾነም ያው መዝሙረኛ ዳዊት “ይሤኒ ላሕዩ እምውሉደ እጓለመሕያው” (ሰው ይኹን እንጂ መልኩ ከሰው ኹሉ አንድም ላሕየ-ተአምራቱ ከሌሎች ቅዱሳን ልዩ ነው) ብሎታል።
እንዲሁም፤ ከምዕራባውያን ልማድ ትምርት እየቀሰመ ያለ ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ ባገሩ ያለውን ጥንታዊ መሠረታዊ ትምርት አጽንቶ ከጠበቀ ከነጮቹ የበለጠ ጥልቅ ዕውቀትን ገንዘቡ ያደርጋል ማለት በቅኔው ተመስጥሯል።


[1] የ“አሐዱ” ሳይኾን የ“ኣሐድ” ተገብሮ ስለኾነ ነው ንባቡን ያነሣኹት።

2 comments:

  1. ለምትመግቡት ትምርት እግዜር መልሶ በመንፈስ ቅዱስ ዕውቀት ያራቃችሁ፡ ለኢትዮጵያ ልጆች ምመኘው ተስፋ ማደርገውም ይህኑ ብቻ ነው። በመወድሱ ሆህያት ላይ የተጠቀማቹትን የዜማ ምልክት፡ እንዴት ማግኘት እችላለሁ?። እመ አምላክ ትስጥልኝ!።

    ReplyDelete
  2. TEBAREKU, DES YEMIL TIMIRT NEW

    ReplyDelete