Wednesday, February 13, 2013

ማብራሪያ

እንደ ኢትዮጵያውያን፥ እንደ ተዋሕዶ ልጆች አኹን የምንገኝበት ዐጸብጺብ (የጭንቅ ጭንቅ) አስገድዶኝ፤ ላፍናቸው ብሻም ባለመቻሌ ሰሞኑን ካንደበቴ የወጡ ኹለት ኀይለ ቃሎች እሊህ ናቸው፦ 

1) ቤተ ክሲያኗ ራሷን እየገደለች ነው።
2) ማኅበረ ቅዱሳን በቅቶታል፤ ክዷል። 

ስለመጀመሪያው፦ እየኾነ ባለው፤ በትክክል ለመናገር፦ እንዲያው ዝም ብሎ በተገብሮ ወይም በደንቦብ (passively or neutrally) እየኾነ ሳይኾን እኛ በገቢር በኀቢር (actively, proactively) እየአኾንነው! ባለው ነገር፤ “መንግሥት እንዲህ አድርጎ፥ እገሌ እንዲህ ብሎ ነው እንጂ…” በማለት ከሓላፊነት የመሸሽ ዝንባሌ በተደጋጋሚ ታዝቤኣለኍ። ይኸውም ጥንት ለአዳምና ለሔዋን ያልበጀ (አዳም በሔዋን፥ ሔዋንም በእባብ ቢያሳብቡ ምክንያታቸው ዋጋ ቢስ ኾኖ “ወኮኑ ቀታልያነ ርእሶሙ” = "ራሳቸውን ገዳዮች ኾኑ" ያሰኛቸው) መኾኑን ሳስታውስ፤ አኹንም ቤተ ክሲያኗ በዋናነት እንመራሻለን በሚሏት የሲኖዶስ አባላት አማካይነት ራሷን ለምእመናን አሙታ ለዐላውያን ነገሥታት ለማኖር እየወሰነች በገዥ በተቃዋሚ ፓርቲ፥ በአቦይ እገሌ በአቶ እገሌ ማሳበብ የማይጠቅም መኾኑን ለመግለጥና ከተቻለ ይኽንን የዕብድ ውሳኔ ለማስቀልበስ በማሰብ ቢመርርም ሐቁን ግልጥ ፍጥጥ አድርጌ ተናግሬኣለኍ። 

ስለኹለተኛው፦ ለሥልጣኑ መደላደል (legitimacy) ከጉልበት በቀር፥ ያእምሮም የሕግም የሕዝብም የምንም መሠረት ማጣቱን የተረዳው የዐላውያን መንግሥት ብዙ አባላት ስላሉት ብቻ ሳይኾን፤ ቀና ቀናዎቹ የተዋሕዶ ልጆች የሚወዱትና የሚያከብሩት እንደኾነ በመገንዝብ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ትክሻ ለመታከክ በሚገባ ዐስቦና አስልቶ በዋልድባ ጉዳይ ላይ እንዲመራመር ሲፈቅድለት የምርምሩን ውጤት ሊቀበል ሳይኾን ስሙን ሊጠቀም መኾኑ ስለገባኝ፤ “ይኸ ማኅበርበዕውቀትም ይኹን አለውቀት ነገ ተነገበስቲያ የጥፋት ኀይሎች መሣሪያ ኾኖልማት ቅብርጥሴበማለት ልባችንን ያደማው ይኾን?” ብየ ስጋቴን ገልጬ ነበር። ምኞቴም ጸሎቴም ግንስጋቴ ከንቱ ኾኖ እንደጉም በኖ እንዲጠፋ” ነበር። ይኹን እንጂ ሰሞኑን ማኅበሩ እያሳየን ባለው ተግባር ምኞቴ እንጂ ስጋቴ ጉም ኾኖ የሚጠፋ አይመስልም። ማኅበሩ ካንዴም ኹለት ሦስቴ ቃሉን በላኣ! ቃሉን በልቷልና፤ ይኽንኑ እየመረረኝም ቢኾን “ካደ” ብየ በተገቢው ኀይለ ቃል ካልገለጥኹት አባላቱን ባግባቡ እስደንግጦ ለራሳቸውም ለ"ታላላቅ ወንድሞቻቸው"ም ጥያቄ እንዲያነሡ የማያስችል ከመኾኑ በተጨማሪ እኔንም በበኩሌ “በከናፍረ ጉኅሉት ልበ ወበልብ” ከሚሸነግሉት የሚደምረኝ ኾኖ ተሰማኝ። “ስለዚህ በቅቶታል፤ ክዷል” ብያለኍ። ማኅበሩ እንዳልበቃውና እንዳልካደ በተግባር ያሳይና እኔን ውሸታም ያድርገኝ። ያን ጊዜ ለዋሸኹበት ንስሐ እገባለኍ።

ሦስተኛም፦ “ለነ አባ እንቶኔ” ያልኍት ራሱን የቻለ ማብራሪያ ይሻ ይኾናል። ነገር ግን ከይቅርታ ጋራ በመጀመሪያው ማብራሪያ ውስጥ የጠቆምኹት ይብቃው። ከዚያ የተረፈው የነሱ ነገር ለጊዜው ይቆየኝ። 
No comments:

Post a Comment