Sunday, April 7, 2013

የደብረ ዘይት ትዝታ!

ታዋቂው ጥንታዊ ፈላስፋ አርስጣጣለስ ሰው በተፈጥሮው ፖለቲከኛ እንስሳ (political animal) ነው ይላል። ያርስጣጣለስ “ወልዱ ዋሕድ ወእሩዩ” (አንድያ እና እኩያ ልጁ፦ the only begotten and co-equal son) እንደኾነ የተነገረለት ዘመናዊ ፈላስፋ ሄግል፤ የሰውን ተፈጥሮኣዊ ፖለቲከኝነት ሲያጦዘው፤ ሰው ኹሉ ካንድ ጠቅላይ መንፈስ (absoluter Geist) ሱታፌ ያለው እንደኾነ አድርጎ አስቀምጦታል።


የለም! ሰው ባለአእምሮ እንስሳ (rational animal) ነው ተብሎ ዐይነተኛ ባሕርዩ በእንስሳነት መደብ ሊታይ አይገባውም በማለት ባርስጣጣለስ እና በዘመናዊውም ሳይንስ አንጻር (በዚህ ረገድ አርስጣጣለስንም ዘመናዊ ሳይንስንም ተቃውሞ) የቆመው ሃይዲገር የተባለ የቅርብ ጊዜ ፈላስፋ ደግሞ፤ ሰው የህላዌ መ-እነሆ-ዊያ፦ ማለትም የህላዌ/የኑሮ ፍሬ ተሸፍኖ ከተቆለለበት ክምር እነሆኝ ብሎ እየወጣ ነዶ በነዶ የሚነሰነስበት ብሎም እየተወቃ የሚፈለፈልበት ምንጥር ዐውድማ (the “There” of Being [Dasein]—the Clearing of Being [Lichtung des Seins]—Openness!) እንደኾነ ይናገራል። የሃይዲገር ዕሳቤ ታዲያ የሰውን በእንስሳ መደብ መገምገም አጥብቆ ይነቅፋል እንጂ ተፈጥሮኣዊ ፖለቲከኝነቱን አይቃወምም። እንዲያውም መጀመሪያ ተማሪው፥ ዃላ ሞጋቹ የኾነው ሌቪናስ እንደሚነግረን “ህላዌ” ራሱን የሚገልጠው በጦርነት መልክ ነውና (Being reveals itself as war) የሃይዲገር “ዳዛይን” የጦርነት ዐውድማ ነው፤ ፖለቲካ ደግሞ ጦርነትን አስቀድሞ አይቶ በኾነው መንገድ የማሸነፍ ጥበብ ነውና የአእምሮ ዐይነተኛ ተግባር ኾኖ ይሰፍናል (“The art of foreseeing war and of winning it by every means—politics—is henceforth enjoined as the very exercise of reason”)።    


እኛም እንደገና በጠየቅን መልካም ነበር፦ “ሰው ምንድር ነው?” ብለን። ምናልባት የቀደሙት እንደሚያስረዱን ይህ የጥያቄ አተካከል ያልተቃና ከኾነም (ሰው ነባቢ አካል [person] እንደመኾኑ “ማን” እንጂ እንደማናቸውም ዕቃ-ነገር [thing] “ምን” ሊባል አይገባውምና) “ሰው ማን ነው?” ብለን ብንጠይቅ መልካም ነበር። በልማድም ይኹን እንደ ሶቅራጥስ አምነንበት “ምንነት” ላይ ሙጭጭ ማለት ከሻንም፤ “የሰው ፍጥረቱ/ባሕርዩ ምንድር ነው?” ብለን፤ አለያም ሌላ የበለጠ ምቹ አገላለጥ ፈልገን ጥያቄኣችንን በተከልንና ክሥተቱን፤ ማለትም ማንነታችንን፤ ሊያሳየን ወደሚችል ግንዛቤ በደረስን እንዴት ባማረ። ነገር ግን ስለማናቸውም ሰው ፖለቲከኝነት በፍልስፍናው አብነት የሚባለውን ለመጠቆም ያኽል ይኸው ይብቃንና ወደሃይማኖቱ አብነት ጎራ ብለን ጥቂት እንጨልፍ፦ ስለሰው ተፈጥሮኣዊ ፖለቲከኝነት።


አዳም የምድር ንጉሥ ነበር፤ ሔዋንም የምድር ንግሥት። እንዲህም ስለኾነ፤ እያንዳንዱ ሰው የአዳምና የሔዋን ልጅ እንደመኾኑ መጠን በ(ገናኛ)ክሂል (potentially) ንጉሥ/ንግሥት ነው። ነገር ግን ባንድ ሕግ የሚተዳደርን አንድ ሕዝብ በአንድ ዘመን በተግባር (actually) የሚመራው አንድ ንጉሥ ስለኾነ፤ አንዱ ሲነገሥ የቀረው የዚያች አገር ሕዝብ ከፊሉ የንጉሡ አሽከር ኾኖ በተዋረድ ያስተዳድራል ከፊሉም ዜጋ ኾኖ ይተዳደራል፤ ባስተዳደሩ የተከፋም ያምፅና ወይ መስተዳድሩን ለቆ ይወጣል አለያም እዚያው ኾኖ ይፈጣፈጣል። እዚህ ላይ የሄግል “What is rational is actual and what is actual is rational” ብሎ ነገር አይሠራም ማለት ነው! ይኽም ሊታወቅ ለአዳም የተሰጠው ሀብት የመንግሥት ብቻ አልነበረም፤ ሀብተ ትንቢትም ተሰጥቶታል፦ መጻኢውን በማየት ጊዜውን ("status quo"ውን) የመተቸት እና የመገሠጥ ሀብት። ሀብተ ክህነትም አለ፤ ሰማያዊውን መንግሥት የማገልገል ሀብት።


ይህም ይህ ነው፤ እንዲህም ስለኾነ ፖለቲካም ኾነ ሃይማኖት እየቅል እየቅል የሚሠሩትን እየሠሩ በሚናበቡበት ደግሞ መናበብ ግድ ነው። በኾነው ረገድ መሠረታዊ ለውጥ እናምጣም ቢሉ በዚሁ መልክ የሚመጣ (differential transformation) ሊኾን ይገባዋል። ዛሬ ባገራችን ግንኖ እንደምናየው ግን እየቅል ሊሠሩት በሚገባው፦ አንዱ በሌላው ጣልቃ መግባት፤ ሊናበቡበት በሚገባው፦ “ምንአገባኽ” መባባል ጥፋት ነው። እንዲሁም በተግባር የዃልዮሽ እየተጓዙ እንዲያው የለውጥ ዐማርኛ በማማረጥ ሕዳሴ ቅብርጥሶ እያሉ ሰውን በወሬ ብቻ ማደናገር ፋይዳ የለውም።


ክህነትም ኾነ ትንቢት እንደ መንግሥት ኹሉ በ(ገናኛ)ክሂል የማናቸውም ደቂቀ አዳም/ውሉደ ሔዋን ሀብት ናቸው። እሊህ ሀብታት በግልጥ በቅባት የተሰጧቸውም፥ ፍት ርት ሲጎድል ድኻ ሲበደል የሚከተለውን ፍዳ በማስረዳት እንደመገሠጥ፤ ከጊዜው ነገሥታት ጋራ ሽር ጉድ ካሉ የሚደርስባቸውን በኢሳይያስ አይተናል። ከሕዝብ የሚነጥል ደዌ ይዳደቃቸዋል/ያገኛቸዋል።   

[ረ ይኸ ነገር፤ በዘመነ ጥናትና ምርምር እንዲህ እንደወረደ እየዘረገፍኍ አንባቢን እንዳላደክም ብቻ ሳይኾን ቁም ነገሩም ጕሥዐተ ልብ እንዳይመስል ፈራኍ። በዚያውስ ላይ ምስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለ! እንግዲህ እዚሁ ይብቃኝና ወደተንሣኹበት ነገር በቀጥታ ልግባ።]

ዛሬ ወደዚች ምክታብ ያመጣኝ ነገር ትዝታ ነው። የኻች ዓምናው በዓለ ደብረ ዘይት ትዝታ። በተለይም በዕለተ በዓሉ ካገራችን ታላላቅ አድባራት ባንዱ ሲያስገመግም ያደረው ማሕሌት፤ ይልቁንም የቅኔው ማዕበል ትዝታ። ዝርዝሩን ላውጋው ብል ጣዕሙን አበላሸው ይኾናልና ለኔው ይቅር።


በዚያች ሌሊት ለደብሩ እንግዳ ስለነበሩ ይመስለኛል ቅኔው (ከዕጣነ ሞገሩ በቀር) የተለቀቀላቸው አንድ መሪጌታ ነበሩ። ርሳቸውም እንዴት ያሉ ዓይናማ ሊቅ ኖረዋል፤ ይኸን የምስጢር ዶፍ አወረዱታ። የምስጢር ዶፉ የፈጠረው ጎርፍ ያጥለቀለቃቸው ሊቃውንትም ልብን በሚመስጥ አቋቋም መቋሚያቸውን እየወዘወዙ ሲቀዝፉት (ሲያዜሙት፥ ሲዘምሙት) መስማትና ማየት የፈጠረብኝን ስሜት ለመግለጥ ከፍሥሓ እና ከሐሴት በላይ ሌላ ቃል ፈልጉልኝ ያሰኛል። ታዲያ ያ ሊቅ ካበረከቷቸው ቅኔዎች መካከል አንዱ የሚከተለው ነበር፦
ለምንት ንብል ጊዜ ይባቤ፤ 
መስተብቍዐ ንጉሥ ልዑል በእንተ ንጉሥ ዘይቤ? 
እስመ ዲበ መንበር ዘዳዊት  
ጥቀ ንጉሠ ነገሥት ኢረከብነ/ኢርኢነ ኀቤ።
 ዐማርኛ፦ 
በዳዊት ዙፋን ላይ   
ፈጽሞ ንጉሠ ነገሥት ሳናገኝ (ሳናይ)፤  
"በእንተ ንጉሥ” የሚለውን ስለንጉሥ የሚጸለይ የምልጃ ጸሎት  
በምስጋና ማሕሌት ጊዜ ለምን እንላለን (እናቀርባለን)?

የቅኔውን ጥልቅ ምስጢር ራሳቸው ባለቤቱ ሲያራቅቁት ሰምቼ በርሳቸው ቃል ባቀረብኍት መልካም ነበር። ይኹን እንጂ፤ ርሳቸው ያሰቡበት መንገድ እቅጩ ይኸ ነው ለማለት ሳልደፍር፤ ሊቁን ባሉበት ይቅርታ እየጠየቅኍና ከተሳሳትኍም ለመታረም ዝግጁ መኾኔን እየገለጥኍ እኔ በወቅቱ ቅኔውን ስሰማው ዃላም በትንሿ ዐቅሜ ሳሰላስለው የተረዳኹትን በጥቂቱ ልግለጠው፦  
ባኹኑ ጊዜ አገራችን መሪ ንጉሥ የላትም። ባፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የተቀመጡት መንግሥት ተብየዎች፤ ራሳቸው ለራሳቸው ባወጡት ስም “ወያነዎች” (ዐመጸኞች) ናቸውና። ተግባራቸውም ቢኾን ያው እንደስማቸው ነው፤ ከቅንነት ጋራ ፈጽመው አይተዋወቁም።ስለቤተ ክርስቲያኗም የሚያስቡት የምትጠፋበትን መንገድ እንደኾነ በጎላ በተረዳ ነገር ታውቋል። 
እንዲህም ስለኾነ "ወኀረዮ ለዳዊት ገብሩ...በየውሀተ-ልቡ...በጥበበ-እደዊሁ" (አገልጋዩ ባለሟሉ ዳዊትን ለመንግሥት መረጠው።... የውሀትን በያዘ ልቡናው...በፈሊጥ ቃሉ መዝ ፸፯፡፸) እንደተባለለት እንደዳዊት በፈቃደ እግዚአብሔር ተሹሞ ሕግን ጠብቆ የሚያስጠብቅ አገርን በቅንነት የሚያስተዳድር ንጉሥ ገና አላገኘንም። አላገኘንምና “በእንተ ንጉሥ”ን ለማን ነው የምንጸልየው? በማለት ጠይቀዋል።

ጥያቄውን ለማዳበር ለብዙዎቻችን ቅርብ የኾነ ነገር ላስታውሳችኍ። ቅዳሴ አስቀድሳችኍ ታውቃላችኍ? መልሳችኍ “አዎ” ከኾነ፤ አኹን የምነግራችኍ በቀላሉ ይገባችዃል። 
በቅዳሴ ጊዜ ልኡካኑ ድርገት ሊወርዱ ሲሉ (ቍርባን ሊያቆርቡ ከመቅደስ ሊወጡ ሲሉ) ከሕዝቡ እየተቀባበሉ የሚያደርሱት መልከአ ቍርባን የሚባል ድርሰት አለ። የዚህ ድርሰት መጨረሻ የሚከተለው ነው፦

እግዚኦ ኵነኔከ ሀቦ ለንጉሥ፤ ጽድቀከኒ ለወልደ ንጉሥ።
አግርር ጸሮ ታሕተ እገሪሁ፤ ዕቀብ ንግሦ ወሠራዊቶ ለንጉሥነ…

ዐማርኛው፦
አቤቱ ፍርድኽን ለንጉሡ ስጠው፤ ጽድቅኽንም ለንጉሡ ልጅ፤
ጠላቱን ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ የንጉሣችን የ...ን መንግሥት ሠራዊቱንም ጠብቅ።
ለዚህም መሠረቱ መዝሙረ ዳዊት ነው። ዛሬ ግን ይኽንን ባዋጅ ሳይኾን በለኈሳስ ለውጠን እንዲህ ነው የምንለው፦ 
እግዚኦ ሰላመከ ሀባ ለሀገር፤ ጽድቀከኒ ለውሉደ ቤተ ክርስቲያን 
አግርር ጸራ ታሕተ እገሪሃ፤ ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ  

ዐማርኛው፦
አቤቱ ሰላምኽን ላገራችን ስጣት፤ እውነትኽንም ለቤተ ክርስቲያን ልጆች፤
ጠላቶቿን ከእግሮቿ በታች አስገዛላት፤ የኢትዮጵያን ሕዝቧንና ሠራዊቷን ጠብቅላት።
በተመሳሳይም አንዳንድ የቅርብ ጊዜ ኅትመቶች "በእንተ ንጉሥ" የሚለውን መስተብቍዕም ኾነ ዘይነግሥ "በእንተ ሀገር" ብለው የድርሰቱን ይዘት በዚያው መሠረት እንዳስተካከሉት አይቻለኍ። ባገልግሎት ግን ባብዛኛው ያው በቃል የተያዘው የጥንቱ ስለሚባል፤ ለንጉሥ የሚቀርበው ምልጃ እንደተዜመ ነበር ከላይ የጠቀስዃቸው ሊቅ ከዚያው አያይዘው በቅኔያቸው ጥያቄውን ያቀረቡት። 

ከዚህም በቀር በመሃይምን አነጋገር የሚባል ተመሳሳይ ጸሎት አለ።

"እግዜር መንግሥትን ይጠብቅ፤ ዐመፀኛን ያውድቅ፤
ሐሰተኛን ያርቅ፤ ፍት ርት ይጠንቅቅ" የሚል።
ነገር ግን ፍርድ የሚገመድለው ዳኛ ሲኾን፤ እንዳሮጌ ቴትሮን በሐሰት የሚቀደደው ነቢይ ሲኾን፥ ለኾዱ አጎብድዶ ፍጡር የሚያመልከው ካህን ሲኾን፤ ድኻ የሚቀማውም ስግብግብ መንግሥት ሲኾን፤ ምን ይባላል? እንዲህ ባለው ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ለማን እንዴት ልትጸልይ ይገባታል?  ወገንተኝነቷ ለሕዝብና ለአገር ከኾነ፤ ይኽንኑ በተግባር የምትገልጠው እንዴት ነው? 
እንግዲህ ሊቁ የጠየቁትን ጠይቀዋል። እኛም እንዲሁ እንጠይቃለን። ፍጥረታችን ስለኾነ። ይኽንና ይኽንን የመሳሰለውን አስተያየት ማቅረብን፥ ፍት ርትን መጠየቅን፥ ለተገፉ ሰዎች ጥብቅና መቆምን፥ ለአበው መነኮሳት መቆርቆርን፥ ወዘተ  "ይኸማ ፖለቲካ ነው" በማለት እንደነውር መቍጠርና ሰው ኹሉ አፉን እንዲለጉም ማሸማቀቅ አይበጅም። እዚህ አደናግሮ መውጣት ቢቻል ስንኳ፤ ዃላ በምጽኣት በዐውደ ሥላሴ በታተቱ ጊዜ መልስ ማጣት አለና። 

...ያቁመነ በየማኑ!!!  


No comments:

Post a Comment