Wednesday, July 31, 2013

ትንሣኤ ግእዝ 2

...የቀጠለ 

 “ትንሣኤ ግእዝ”፦ በባዕድ አገር 


ኹለት ስሞች ልስጣችዅና ጎጕሏቸው (ታሪካቸውን በጕግል አማካይነት እየጎለጎላችኍ አውጡት ማለቴ ነው፤ እንድታነቡት)፦ ሂዮብ ሉዶልፍን እና ኦገስት ዲልማንን (Hiob Ludolf and August Dillmann)። እሊኽ የአለማኝ (የጀርመን) ምሁራን፤ በምዕራቡ ዓለም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መሥራች እና ዐዳሽ ተብለው ይታወቃሉ ፤ እንደስማቸው ተራ። ይኸውም ሉዶልፍ በዘመናዊው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ሃይማኖት፥ ታሪክ እና ባህል፥ ቋንቋዋን ግእዝንም በስፋት በማስተዋወቅ፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ያውሮፓ የትምርት ማእከላት በምር እንድትጠና ያስቻለ ሲኾን፤ በጊዜ ብዛት ጥናቱ እየቀዘቀዘ ሲመጣ፤ ዃላ ዲልማን ተንሥቶ ምርምሩ እንደገና እንደዐዲስ እንዲያብብ አድርጎታልና ነው። 
ሂዮብ ሉዶልፍ

የሚገርመው ነገር ኹለቱም ሊቃውንት ለዚኽ የበቁት፤ የግእዝን አገር ኢትዮጵያን ሳይረግጡ መኾኑ ነው። ዲልማንማ ከአንድም ኢትዮጵያዊ ጋራ ተገናኝቶ አያውቅም። ከጀርባውም ከፊቱም ኾነው የግእዝን አእምሮ የገለጡለት በልዩ ልዩ ምክንያት ካገራቸው ወጥተው በመላው አውሮፓ ተበትነው የሚገኙት የብራና መጻሕፍት ነበሩ። ሉዶልፍ ግን ከጀርባው ከነበሩት መጻሕፍት በተጨማሪ አንድ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ፊት-ለ-ፊት ቃል-በ-ቃል አስተምረውታል። አባ ጎርጎርዮስ የተባሉ የመካነ ሥላሴ ሊቅ።[1] አባ ጎርጎርዮስ በሉዶልፍ ግብዣ በጀርመን የነበራቸውን ቆይታ ፈጽመው ወደ ሮም ከኼዱም በዃላ ስንኳ ሉዶልፍን በመልእክት ማስተማራቸው አልቀረም።
አባ ጎርጎርዮስ
ከዲልማን በዃላ በዚያው በአልማንያ (በጀርመን)፦ እነ ኤኖ ሊትማን፥ ካርል ባዞልድ፥ ኦይገን ሚትቮኽ ወዘተ፥ በፈረንሳይ፦ እነ ደ’አባዲ፥ በጣሊያን፦ እነ ኮንቲ ሮሲኒ፥ ኢግናሲዮ ጕይዲ፥ በእንግሊዝ፦ እነ ሌስላው ወእለተርፉ (ወዘተ[ርፉ]) በራሽያም በሌሎችም አገሮች ብዙዎች ትምርቱን በትጋት ቀጥለውበት ስለነበር፤ ምንጩም እየሰፋ ጥቅሙም እየጎላ ኼዷል። ስለኾነም ባኹኑ ጊዜ በሀምቡርግ (እነ ኡሊግ)፥ በማይንዝ (እነ ክሮፕ)፥ በበርሊን (እነ ፎይግት)፥ እንዲኹም በሮምም፥ በፓሪስም፥ በሎንዶንም፤ እንደ ራሺያ ቼክና ፖላንድ ባሉ የምስራቁ ክፍሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር፤ ባማሪካም፤ በግብጽም በሶርያም፤ ምናልባት በጃፓንና በሌሎች የሩቅ ምስራቅ አገሮችም በሚገኙት ጭምር ለጥናቱ ወንበር ዘርግተው መምህር ቀጥረው እያስተማሩ ያሉ ብዙ ናቸው።
ኦገስት ዲልማን
ይኽም ይኽ ነው፤ ይኹንና በእኔ አስተያየት ከውጮቹ ምሁራን እንደ ሮጀር ካውሊ ያለ ቀድሞም አልተነሣ ወደፊትም መነሣቱን እንጃ። የርሱ ባጭር መቅረት ሲቆጨኝ ይኖራል። የሥራው ፍሬ ሊታወቅ ፈለጉን የተከተለችው ዴኒሿ (ዴንማርካዊቷ) ሊቅ ኪርስተን ስ. ፔዴርሰን፤ ለኢትዮጵያ እምነት ክብር በቅታ ከሌላ ሌላው በተለየ ዳዊቱን ከነአንድምታ ትርጓሜው ሳይቀር አሳምራ አጥንታዋለች፤ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምንኩስና መዓርግም በመብቃቷ እማሆይ ክርስቶስ ሠምራ ተብላለች።


እማሆይ ክርስቶስ ሠምራ (ፔደርሰን)  
“ትንሣኤ ግእዝ”፦ በገዛ አገሩ  
ይኸ ኹሉ ሲኾን ግን፤ እኛ “በገዛ ዳቧችን ልብ ልቡን እንድናጣ” ማን እንደፈረደብን ሳናውቀው፤ ግእዝ ካገሩ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተሰዶ ኑሯል። አኹንም እንደተሰደደ ነው። ምክንያቱን በማተት ላደክማችኍ አልሻም። ኹናቴው ግን እጅግ የሚያሳዝን መኾኑን ማንም አያጣው። 
አንጋፋው የዐዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገና በቀድሞ ስሙና ክብሩ እንደነበረ፤ ከዐይናሞቹ ሊቃውንት አንዱ ፕሮፌሶር ጌታቸው ኀይሌ፦ በተለይ በታሪክ እና ሥነጥበብ ክፍል የሚያጠኑ ተማሮች ግእዙን በጥልቀት ማወቅ ይጠበቅባቸዋልና ለዚኹ እንዲረዳቸው ቅኔ ይማሩ በማለት የሰጡት ማሳሰቢያ ሰሚ አጥቶ ቀርቷል። ይባስ ብሎም፤ ላማርኛ ድጋፍ በሚል ብቻ ለይስሙላ ያኽል ላይ ላዩን የሚሰጠው የግእዝ ትምርት ስንኳ “ተነሽ ወዳቂውን” አስተካክሎ በማያነብ አስተማሪ እጅ ወድቆ እንደነበረ ባንድ አጋጣሚ እኔው ራሴ ታዝቤኣለኍ።[3]
በሀምቡርግ ከተማ  ዐይናማውን ሊቅ ጌታቸው ኀይሌን ለማየት በቃኍ!
ከደግ  ባለቤታቸው ጋራ፤ ዐብረንም የመርከብ ላይ ጕብኝት አደረግን።

ይኹንና አኹን አኹን አንዳንድ ዐይናሞች የግእዝ ምሁራን በግቢው ውስጥ መግባታቸው ለዩኒቨርሲቲው ግርማ ኾኖታል። እንዲያውም ጨርሶ ውጭ ለውጭ ሲዞሩ ከማንጋት በውድቅት ሌሊትም ቢኾን እቤት ገብቶ ማደር እንደሚሻል ዅሉ፤ ምናልባት ግእዝም የማታ ማታ ባገሩ እንዲከበር ለማስቻል የሚበጅ “ፊሎሎጂ” የሚባል ትምርት ተጀምሮ ተማሮችን በማሠልጠን ላይ ይገኛል። 
  
ግን፥ ግን... እኔ ደግሞ አበዛዋለኍ!
የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወዳገሬ ኼጄ ለኹለት ወራት ያኽል ቆይቼ ነበር። ዘመደ ብዙ ጠላው ቀጭን ነው የሚባለው ነገር ደርሶብኝ፤አንዴ ደሴ፥ አንዴ ወረይሉ፥ ኹለቴ መቀሌ እያልኍ እግሬ እስኪቀጥን ከዞርኍ በዃላ፤ በመጨረሻው ዐዲስ አበባ ገብቼ ወደመጣኹበት ለመመለስ በረራየን በምጠባበቅበት ሳምንት አንድ ወዳጄ ያስተዋወቀኝ ዐይናማው ፈላስፋ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ያላቅሜ እንዲያው በቸርነቱ በዩኒቨርሲቲው የመማሪያ አዳራሽ ለተማሮቹ እና ፍላጎት ላላቸው ምሁራን ስለኢትዮጵያዋዊው ያስተሳሰብ ፈለማ ጥቂት እንዳወሣ ዕድል ሰጠኝ።
 ተራ የፍልስፍና አስተማሪ ሳይኾን፤ 
እንዲኽ ያለ ምጡቅ ፍልሱፍ (የምር ተፈላሳፊ) በማየቴ እንዴት ተደሣኍ!
በእውነቱ እጅግ ጥሩ ጊዜ ነበር። በወቅቱ የነበረውን ውይይት ከተከታተሉት መካከል ታዲያ አንዱ የሸገር ኤፍ ኤሙ አቶ አንዱዓለም ነበርና፤ ርሱም የሸገር ካፌ እንግዳ አድርጎኝ ድምፄን ለመጀመሪያ ጊዜ በራዲዮ ሰማኹት! (ለመጨረሻም ይኾን? ረ አይኹንብኝ፤ ገና ብዙ እማሰራጨው ይኖረኛል!)። 
ደግሞ እንጂ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ክፍል ያሉ ሊቃውንት ወዲያው አከታተሉና እስኪ አንድ ምሽት ላይ ተገኝተኽ በፈለግኸው ግእዝ ተኮር ጕዳይ እንነናገር ቢሉኝ፤ ከላይ በፊሎሎጂው መስክ ተጀመረ ያልዃችኹን ጥቂት አፍኣዊ ዕድገት ከማወዳደስ ይልቅ የሚቀረውን ዐይነተኛ ውሳጣዊ ጕዳይ ማስታወስ ይሻላል ብዬ፤ለውይይት መነሻ ባቀረብዃት አጭር ጽሑፍ እንዲኽ አልኹላችዃ፦ 
... 
While appreciating the numerous serious philological works that have been done on Geez literature for more than a century now[1] and craving the continuation of such a noble task in an even more concerted manner in the future, I would like to show the necessity to embark on further undertaking that goes beyond anointing, as it were, the dead body of Geez with sweet spices. Particularly, I will point up the need—or, shall create one, if it probably was held to have never been felt—for constructively attending to Geez/Ethiopic mind as it has been manifesting itself throughout the millennia-old history of this great nation...[1] I know how surprisingly young Geez philology is at the universities in its own homeland. But I consider here the works on Geez literature since Dillmann, if not since Ludolf—the true lovers of both the language and of the minds that enriched it as they had been nurtured by it.
ሙሉ ጽሑፉን እዚኽም ለጥፌው ነበር። ከዚኽ ቀደም ያላያችኹት ኾኖ አኹን ለማንበብ ለምትሹ፤ መገናኛው እነሆ፦Attending to Geez Mind in our Age: An Indispensable Approach to Regain the Ethiopian Perspective.

ይኽም ይኽ ነው፤  በውይይቱ ታዲያ ብዙ ገንቢ ዐሳብ፥ ብዙ ትምርትም አገኘኹበት። ከዚያ ተመልሼ ቶሮንቶ ስገባ ግን፦ ድንዝዝ!
አኹንም ይቀጥላል…[1] ሉዶልፍን አባ ጎርጎርዮስ እንዳስተማሩት፤ በስሙ ከሚታወቁትም መጻሕፍት ዋናዎቹ ከርሳቸው የተነገረውን እንደወረደ ያኽል ገልብጦ ያሰፈራቸው መኾኑ እየታወቀ፤ ርሱን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር “መሥራች” ብሎ እሳቸውን “መረጃ አቀባይ” (informant) ማለት እንዴት ያለ ፍርደ ገምድል የሙያ ድልድል እንደኾነ አንባቢ ያስተውል። በነገራችን ላይ የዛሬ ዐርባ፥ ዐምሳ ዓመት ገደማ ይኽ ጉዳይ የቆጫቸው ዐይናማ ኢትዮጵያዊ ምሁር (ጌታቸው ኀይሌ) ነገሩ አግባብ አለመኾኑን ለፈረንጆቹ በግልጥ ቋንቋ ያስረዱበትን አንድ ውብ ጽሑፍ ማንበቤ ትዝ ይለኛል።  [Getatchew Haile, Ethiopian Studies in the Framework of African Studies = Cimarron Review (Oklahama 1970) 9]  
[3] የፕሮፌሶር ጌታቸው ጽሑፍ ርእስ፦"Ethiopianization: Its Meaning and the University's Role in the Ethiopianization Process" የሚል ሲኾን ያቀረቡትም ለ "Conference on the Role of a University in CON Developing Country (Addis Ababa 1967)" ነበር።ዃላ በ80ዎቹ መጨረሻ ወይም በ90ዎቹ መጀመሪያ ገደማ ይመስለኛል፤ ገና የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ እንደነበኍ አንድ ዐይነ ስውር የቋንቋ ተማሪ ለውጤት ማሟያ ግእዝ ይማር ኖሮ ፈተናው ሲደርስ ጥያቄ እንዳነብለት ወደ ስድስት ኪሎ ለምኖ ወስዶኝ ለማንበብ ተቀምጫልኍ። በጥያቄ ወረቀቱ ላይ ከሰፈሩት ነገሮች ታዲያ ለተወሰኑ ጥያቄዎች መሠረት በነበረው ምንባብ አንዳንድ የታይፕ ስሕተት እንዳለበት ግእዝ ጠንቅቆ ለሚያውቅ አንባቢ በግልጥ ይታያል። በተለይ አንድ መሥመር ላይ የነበረ ስሕተት ካልተስተካከለ በቀር ላንድ ጥያቄ መልስ ከቀረቡ አማራጮች አንዱንም ለመምረጥ አያስችልም። ታዲያ እኔም የተጻፈውን አንብቤ ሳበቃ፤ “የለም፤ ይኸ እንዲኽ ለማለት ተፈልጎ ነው፤ የታይፕ ስሕተት ይመስለኛል” ስል፤ ተማሪው አስተማሪውን ጥራና ይኽንኑ እንንገረው አለኝ። አስተማሪው ተጠርቶ ሲመጣ ግን ስንኳን ስሕተቱን ሊገነዘብ አስተካክሎ ማንበብ ሲሣነው በመታዘቤ በዩኒቨርሲቲው ዐፍሬ ወጥቻለኍ። 

No comments:

Post a Comment