Friday, July 26, 2013

ትንሣኤ ግእዝ


ግእዝ፦ የሞተ ወይስ ለጥፋት የቀረበ ቋንቋ?
(Is Geez a dead language or an endangered one?)

የመርበብቱ ዓለም ራሱን የቻለ መኖሪያ ቦታ ነው ባይባልም፤ ብዙ ዓይነት ማኅበረሰቦች ብዙ ዓይነት ጕዳይ የሚጐድዩበት ልዩ ልዩ ተግባር የሚያከናውኑበት የማይናቅ ክፍለ ዓለም መኾኑ ግን የሚያጠራጥር አይመስለኝም። በበኩሌ ይኽንኑ ዐዲስ እውነታ በፈረንጆቹ 2002 ገደማ በምር ስለተገነዘብኍ፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምርት እና ሥራት በዚኹ ክፍለ ዓለም (ማለትም፦ በመርበብቱ ዓለም፤ i.e., on the internet) በስፋት እንዲወከል ፍላጎት ተቀሰቀሰብኝ። እናም ወዲያውኑ “ሊቅነት በኢትዮጵያ” ምን ይመስል እንደነበረ ለመረዳት አንድ “Traditional Ethiopian Scholarship” የተሰኘ “የያሁ ግሩፕ” አቁሜ ከተወሰኑ ወዳጆች ጋራ ርስ በርስ ስንማማር ቆይተናል።

ዃላ ጕዳዩን ዅሉም እየተረዳው ሲመጣ፤ በዚያውም ላይ ኪኑ (the techology) እያደገ ዘርፉም እየበዛ ሲኼድ ለመረጃ ያኽል የሚደረጉ ተመሳሳይ ውይይቶች አስተናባሪኣቸውም ተሳታፊኣቸውም በእጅጉ ጨምሯል። እኔም ይኽንኑ ስመለከት፤ በኾነው ነገር ከመደሣት ጋራ ምናልባት ጠለቅ ያለ መሠረታዊ ትምርት መስጠት ይቻል እንደኾነ ለመሞከር ይኽንን የመሥመር ላይ ምክታብ (online blog) ጀመርኍ። እንዳጀማመሬ ግን በሚገባው መንገድ አልገፋኹበትም። ምክንያቱን በከፊል “እየየም ሲደላ ነው” የሚለው አባባል የሚገልጠው ሲኾን ቀሪውን ለሌላ ጊዜ እናቆየውና አኹን ወደተነሣኹበት ጕዳይ ላምራ። 

“ትንሣኤ ግእዝ”፦ መጽሐፍ 


እውነትም ለካ ቀረብ ብሎ ግእዝን በጥልቀት ለመማር ጕጕት ያላቸው ብዙዎች ኖረዋል! ከእነሱም መካከል ቀደም ሲል የግእዝን ትንሣኤ ለማየት ጽኑዕ ፍላጎት ያደረበት አንድ መምህር በገሀዱ ዓለም የሰበሰባቸው ወጣቶች፥ በዘመኑ ጥበብ የሠለጠኑ ነበሩና “ግእዝ በመሥመር ላይ”ን በደሥታ የሚከታተሉት ከመኾኑም በተጨማሪ፤ በዚኹ በመርበብቱ ዓለም “ፌስቡክ” በሚባለው ከተማ “ለግእዝ ቤተሰቦች” መሰባሰቢያ የሚኾን ጎጆ ሲቀልሱ እኔንም ጋብዘው አስገቡኝ። ረ እንዲያውም አሳላፊ ሊያደርጉኝ ከጅሏቸው ነበር፤ እኔው “እስኪ ለጊዜው ይቆየኝ” ብየ “አይኾንም” አልዃቸው እንጂ።  

ይኽ ከኾነ ብዙም ሳይቆይ እሊኽን ብሩሃን ደቂቀ ግእዝ የሰበሰባቸው ያ ወጣት ምሁር አዘጋጅቶ ያቀረበውን ይግእዝ ማስተማሪያ መጽሐፍ “ትንሣኤ ግእዝ” ብሎ ሰይሞት አየኹ። ማለፊያ ስያሜ ነው። ለጥንታዊው ቋንቋችን ለግእዝ ለጥንታዊቷም አገራችን ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ያለንን ጕጕት ይገልጣልና።  (ግእዝ ማለት ኢትዮጵያ ማለትም ስለሚኾን። “እስከ ዮም ትትፌሣሕ ወትትሐሠይ ግእዝ” እንዲል ስንክሳር። ይኽም፦ “ግእዝ=ኢትዮጵያ እስከዛሬ ድረስ ትደሣለች/ደሥ ይላታል” ማለት ነው።) 
 
“ትንሣኤ ግእዝ”፦ ክርክር


ይኹንና “ትንሣኤ ግእዝ” የሚለው ሐረግ ግን ረዘም ያለ ታሪክ አለው። ገና ከደርግ ዘመን በፊት፤ ዘመናዊ ትምህርት በመላ አገራችን “ኹሉ በኹሉ” እየኾነና ጥንታዊው የጥበብ ቅርሳችን እየተናቀ ሲመጣ፤ አካኼዱ ያላማራቸው ሊቃውንት ኹናቴውን ለመቀልበስ ይመስላል፤ ይቅርና የውጭ ቋንቋ ዐማርኛም ስንኳ ያለግእዝ ርዳታ በራሱ ለኑሯችን በቂ እንዳልኾነ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ክርክር አድርገው ነበር። የክርክሩን ይዘት በመጽሔት አሳትመው ለሕዝብ ሲያቀርቡ ታዲያ፤ መጽሔቱን ለግእዝ ትንሣኤ ያላቸውን ምኞት በሚገልጥ መልኩ “ትንሣኤ ግእዝ” ብለው ሰይመውታል።  


“ትንሣኤ ግእዝ”፦ ማኅበር 
ይኽም ይኽ ነው፤ እኔም ከጀርመን አገር ተመልሼ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማስተምርበት ጊዜ፤ አንድ ዐይናማ ወጣት የቅኔ መምህር ይዘን ከተወሰኑ ወንድሞች ጋራ በመኾን ሥራዬ ብሎ የግእዝን ትምርት የሚያስፋፋ ማኅበር ለማቆም ወሰንን። ስሙን ማን እንበለው በሚል ዐሳብ ስናወጣና ስናወርድ፤ ከዚኽ በላይ ያሰፈርኹትን ታሪክ መነሻ በማድረግ “ትንሣኤ ግእዝ” እንበለው የሚል አስተያየት ሰጠኹ። አያይዤም ግእዝ ለቋንቋው ብቻ ሳይኾን ላገሪቱም መጠሪያ መኾኑን ለማስታወስ ሞከርኹ። ይኹን እንጂ ጕዳዩ ብዙ አከራከረን። ከረዥሙ ባጭሩ፤ ጥያቄው ነጥሮ ነጥሮ እንዲኽ የሚል ኾነ፦ ግእዝስ ኾነ ኢትዮጵያ ሞተዋልና ነው ወይ “ትንሣኤ ግእዝ” የምንለው?   
እንደመልስ የቀረቡትም ዐሳቦች ባጭሩ እሊኽ ነበሩ፦ 
 1. መነሣት’ኮ ግዴታ ከሞት አይደለም፤ ወድቆም መነሣት አላ።
 2. አዎ፤ ሞተዋልና! ለመኾኑ ግእዝስ ኾነ አገሪቱ አሉ ሊባል ነው?
ከብዙ ሙግት በዃላ ዅላችንን ያስማማን አስተያየት ግእዝም ኾነ አገራችን ብያ (=already) እንደሞቱም ነገር ግን እንዳሉም የሚቆጠሩበት ኹናቴ መኖሩ ነበር። ስለዚህም ከመካከላችን አንዱ፦ በከነዓን እንደሞተ ሲቆጠር በግብፅ በሕይወት በነበረው በዮሴፍ ምሳሌነት “ምውት በከነዓን ወሕያው በምድረ ግብፅ” ብሎ ግእዝንም አገራችንንም ገለጣቸውና ዐተታችንን በዚያው ገታነው።   
ስለዚኽም የማኅበሩ ስም “ትንሣኤ ግእዝ” እንዲኾን ወስነን ሥራ ለመጀመር ከፍትሕ ሚንስቴር ፈቃድ ጠየቅን። ቢሮም ተከራይተን እንደ ወንበር ጠርጴዛ ያሉ ቈሳቍሶችን አሟላን። ሥራውን ልንጀምር ጫፍ ላይ ስንደርስ ግን በማኽሉ ምርጫ ዘጠና ሰባት ከች አለና ትርምስ ተፈጠረ። ምንም ስንኳ ፍትሕ ሚንስቴር ፈቃዱን ቢሰጠንም፤ ትርምሱ ጋብ ከማለቱ እኔ በትዳር ምክንያት በግዴታ ውዴታ ወደካናዳ መጣኍና፤ ሌሎቹም በየበኩላቸው በግል ሥራዎቻቸው ተወጠሩና፤ የማኅበራችን ነገር በምኞት ቀረ።


ይኹን እንጂ ኹላችንም በየበኩላችን ለግእዝም ኾነ ላገራችን ከመሥራት አልቦዘንንም። የሌሎቹን ላቆየውና በበኵሌ፤ ያለችኝን ጥቂት መክሊት ለማጋራት የሚያስችለኝን መንገድ ለመቀየስ እየታገልኍ አለኍ። እጅግ ታላቅ ተስፋ የጣልኹበት አንዱ እና ዋናው መድረክም ይኸው “ግእዝ በመሥመር ላይ” የተሰኘው ምክታብ ነው።

ይቀጥላል...  (በፈቃደ እግዚአብሔር ባጭር ጊዜ 'ብሥራት ቢጤም' አሰማችዃለኍ)…


5 comments:

 1. እግዚአብሔር፡ያበርታዎ!።ድንግል፡ወላዲተ፡አምላክ፡በርሷና፡በልጇ፡ኪዳነ፡ምሕረት፡ትደግፍዎ፥ታጥናዎ!።ወንዕቀብ፡ለመጻኢ፡ብሥራት!።[??]

  ReplyDelete
 2. This comment has been removed by the author.

  ReplyDelete
 3. በርታ መናርን እንፈልጋለን! እግዚአብሔር ብርታትና ጤናን ይስጥህ!

  ReplyDelete
 4. God bless you. Push the hard work to revive the latin of all the semitic languages of Eritrea and Ethiopia.

  ReplyDelete