Thursday, August 8, 2013

ትንሣኤ ግእዝ 3

 “ትንሣኤ ግእዝ”፦ ሥሯጽ (በእንተ ርእስየ)
...የቀጠለ
ባለፈው “ድንዝዝ” እንዳልኍ ስጠቁማችኍ ሳታዝኑልኝ አትቀሩም። “ለምን” ብላችኹም ጠይቃችኍ ይኾናል። እውነቱን ልንገራችኍ? ለመደንዘዜ ዋናው ምክንያት፦ አገራችን የምትገኝበት፥ ቤተ ክሲያናችንም ያለችበት አሳዛኝ ኹናቴ ነው። ዝርዝሩን ላቆየው። ይኽም በመኾኑ አንዳንዴ ነፍስ ስዘራ እንኳ፤ በዚያው ነፍስ በዘራኹበት ጊዜ ስላለው ያገራችን እና የቤተ ክሲያናችን ጠቅላላ ኹናቴ እንጂ፤ ስብስብ ብየ በተለይ ስለግእዝ ብቻ ለማሰብ አልቻልኹም (በማርች 2012 መጨረሻ እና በቀጣዩ ወር ካደረግኹት አንድ ጥረት በስተቀር፦ ይኸውም "የግእዝ ንባብ በቀላል ዘዴ"ን አዘጋጅቼ፤ ለቶሮንቶ ነዋሪዎች ለማስተማር ያደረግኹት ሙከራ ነው)። 


እንዲያውም በዋናነት የግእዝን ትንሣኤ እንድናይ ትውልዱን በመሥመር ላይ (online) ለማሠለጥ በተሠየመው በዚኽ ገበታ ስንኳ፤ ሰማይ ከምድር እንዲርቅ እንዲኹ ክብራቸውም ኾነ ማረጋቸው ከእኔ እጅግ የሚርቁትን አካላት ሳይቀር የሚተቹ ዐሳቦችን አቅርቤበታለኍ። በተለይ ከሊኽ አካላት ጋራ በማነጻጸር “ለመኾኑ አንተ ማን ነኽና እነሱን ትተቻለኽ?” ብላችኍ እንደኾነ (እንዲኽ ብለው የጠየቁኝ አሉ)፤ እነሱም ኾኑ እኔ በግልጥ ያስቀመጥናቸው ኅልያት (thoughts) በጽድቅ (በእውነት) መሠረት ላይ የጸኑ የመኾን አለመኾናቸው ነገርና ለሕዝብ የሚኖራቸው ጠቀሜታ ወይም ጉዳት እንጂ በሀብት በማዕርግ መበላለጣችን ስንኳን በቅድመ እግዚአብሔር እዚኽም ያለው ፋይዳ ጥቂት ይመስለኛል።[1]

ለማንኛውም እኔ፦ ኢትዮጵያዊ ትውፊታችንን ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል እና ትውልዱን ባየር ላይ ለማንሳፈፍ ግልብ ዐተታ ሲያትት፥ ረቂቅ ተንኮል ሲሸርብ የማየውን ኹሉ--ማንም ይኹን ማን (ሌላውን ትታችኹት ከፍ ብሎ አንገት ዝቅ ብሎ ባት ሊቆርጥ የሚችል ንጉሥም/ምኒስቴርም ቢኾን)--በድኻ ዐቅሜ ልታገለው እንጂ በቸልታ ላልፈው አልሻም። ይልቁንም፦ በስም እና በሥልጣን መስፈራርቾ ጭምር በተማሮች እና በሕዝብ አእምሮ በግድ እንዲሰገሰጉ የኾኑ ማናቸውንም ሥር-ነቀል መመሪያዎች፥ ጠማማ ዘገባዎች፥ መሠረተ-ቢስ ዐተታዎች የነገራቸውን ቁልጵስጵስ ገጸ-ንባብ በርቅሶ ምስጢራቸው ውስጥ በመግባት እኩይ ዐላማቸውን የሚደቁስ የብርዕ ቦሎታ እያዘጋጀኹ ያለኹ እንጂ፤ በሌለ ወይም በማይገባ ነገር ላይ በከንቱ ቀለም የምደፋ ጠብጣባ፟ ባለሙያ (ችኩል ጸሐፊ) እንዳይደለኹ ለመጠቆም ያኽል፤ ከያዝኹት ርእሰ ጕዳይ በማይርቅ መንገድ ስለራሴ ትምርት ባጭሩ የሚከተለውን ለማለት እወዳለኹ።

በልጅነቴ የተማርኩት የቤተ ክሲያን ትምርት እስከ ወንጌለ ዮሐንስ ብቻ ነበር። ወዳስኮላው ትምርት ቤት ስገባ ዳዊት ስንኳ አልደገምኩም። በራማ ኪዳነምሕረት ገዳም ይኖሩ የነበሩት አያቴ አባ[2] ተክለ ጻድቅ ወልደ ማርያም ከስንት ዓመት አንዴ እየመጡ ሲጎበኙን ከብዙ የልጅ ልጆቻቸው መካከል ቢያንስ አንዱን ወደገዳም ወስደው የቤተ ክህነት (መንፈሳዊ) ትምርት ለማስተማር በነበራቸው ጕጕት፤ ከሌሎች ወንድሞቼ ጋራ ድመፃችንን እና ትሕትናችንን ሲያወዳድሩ እኔን የመምረጥ አዝማሚያ ቢያሳዩም፤ መልሰው ምን እንደሚያስቡ ከግምት ባለፈ በርግጥ በማላውቀው ኹናቴ ማንንም ሳያስከትሉ ወደበአታቸው ይመለሳሉ። በመጡ ቁጥር ያው ነው። 

አባ ቀኛዝማች ተክለ ጻድቅ ወልደ ማርያም
ከምንኩስናም በዃላ ዐርበኝነቱ እንደገና ሞከር አድርጓቸው ነበር። ይኸውም የገዳማቸውን የራማ ኪዳነ ምሕረትን ዐጸድ የደርግ ካድሬዎች ለልማት ይኹን ለኾነው ጉዳያቸው ሊቆርጡ ያስባሉን ሲሰሙ፤ "እኔን ገድለው ይቆርጣሉ" በማለት መሣሪያየን አምጡልኝ ብለው ዘብ በመቆማቸው፤ ካድሬዎቹ መግደል ባይሳናቸውም ልብ ገዝተው ዐሳባቸውን ሰርዘዋል።

አያታችን ማረፊያቸው እንደቀረበ ሲረዱ፦ ልጃቸው እናቴ ወ/ሮ አሰፋሽ ተክለ ጻድቅ በልጅነቷ ዳዊት ስለደገመች ለእሷ ራሳቸው ሲጸልዩበት የነበረውን የሚያምረውን ያስመራ ዳዊታቸውን እና አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የታተመውን የውዳሴ ማርያም አንድምታቸውን፣ በዘመናዊው ትምርት ጥቂት ገፋ አድርጋ ለተማረችው ለአክስቴ ለወ/ሮ ሰዋስው ተክለ ጻድቅ የታሪክ እና የምክር መጻሕፍቶችን፣ በመጠኑም ቢኾን የክህነት ትምርት ለነበረው እና ደግነቱን፣ ጸሎተኝነቱን ለሚወዱለት ለአባቴ ለአቶ ታደሰ ፈለቀም በብራና የተጻፈውን መልክአ ጉባኤ እና ሌሎች የጸሎት መጻሕፍታቸውን ሲያወርሱ፤ በርሳቸው ስም ለሚጠራው ለወንድሜ ለክፍለ ያዕቆብ ተክለ ጻድቅ ደግሞ የመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ እንዲደርሰው አድርገው ነበር። 

በርግጥ ወንድሜ ክፍለ ያዕቆብ ገና የኹለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በጀመረው የመጠጥ ሱስ ላይ ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ ሲማር ጫት የመቃም እና ሲጋራ የማጨስ ክፉ ልማድ ደምሮበት ካባታችን በመቃቃሩ፤ አባታችን በስጨት ሲል “ይኸ ከሀዲ” እያለ ቢጠራውም፤ አንዳንድ አስጨናቂ ነገሮች ሲያጋጥሙት “ያባቴ የቀኝአዝማች ተክለጻድቅ አምላክ አለኝ!” ሲል እሰማው ስለነበረ፤ ሃይማኖቱን ሙጥጥ አድርጎ የካደ እንዳልነበረ ዐውቃለኍ። ኾኖም ግን ያወረሱትን መጽሐፍ ቀድሞ ወደገዳም ሲገቡ ሰጥተውት እንደነበረው ጠበንጃ በስማቸው የሚጠራባቸው ያያቱ ማስታወሻ አድርጎ ከሚያከብረው በቀር፤ በይዘቱ አልተጠቀመበትም። እንዲያውም (የኹለቱንም ነፍስ ይማርና) ርሳቸው ባረፉ በስምንት ወራቸው ስለተከተላቸው፤ ያ የመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ ያለባለቤት እግድግዳ ላይ ተንጠልጥሎ ቀረ።እኔ ግን ያሥረኛ ክፍል ትመርቴን ካጠናቀቅኹ በዃላ ነው እንደገና የቤተ ክሲያን ትምርት ያማረኝ። በወ/ሮ ስሂን ት/ቤት የ10+3 መርሐ ግብር የሙያ ተማሪ ኾኜ ጧትም ተስያትም ት/ቤት በምውልበት በዚህ ወቅት ያደረብኝን የቃለ እግዚአብሔር ጥም ለማቀዝቀዝ ማታ ማታ የቃል ትምርት ስማር ከመስተጋብእ ደርሼ ነበር። ዳዊትም በበጋው ከዘመናዊ ትምርት ለመሻማት የቻልኹትን እና በክረምት የማገኘውን ዘና ያለ ጊዜ በመጠቀም ደገምኹና ጥሩ አንባቢ ለመኾን በቃኹ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ገድላገድልና ድርሳናትንም ማንበብ የዘወትር ልምዴ ነበር። እንዲህም ስለኾነ በመምህራን እጥረት ምክንያት እኔም እንዳቅሜ (“እምይትጎል” = እንዳይታጎል ያኽል) ቃለ እግዚአብሔር ለማስተማር ስመደብ፤ በየሰንበታቱ የሚሰበኩትን መዝሙራት ዐይነተኛ ምስጢር ይዤ ለመቅረብ እንድችል ለወንድሜ ተሰጥቶት የነበረውን የመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ ከተንጠለጠለበት ግድግዳ ላይ አውርጄ ከማኅደሩ እያወጣኹ መመልከት ጀመርኍ።


መጽሐፉ የዳዊቱን ምንባብ በግእዝ አንብቦ፤ ትርጕሙን “አንድም” እያለ ባማርኛ የሚተነትን በመኾኑ ለፈለግኹት አገልግሎት በጣም ጠቅሞኝ ነበር። ነገር ግን ባማርኛው ትርጕም ውስጥ አንዳንድ ጥቅሶችን የሚያስገባበት ምክንያት ሲኖር በግእዝ ይጠቅሳቸውና ሳይተረጕማቸው ስለሚያልፍ በነዚያ ጥቅሶች ማስረጃነት የሚተላለፈው መልእክት ሳይገባኝ እየቀረ ተቸገርኍ።

በዚህ ጊዜ ነበር ቅኔ የመማር ፍላጎት የተጫረብኝ። ተጭሮብኝም አልቀረ፤ ፍቅሩ እየወዘወዘኝ የነበረውን የዜማ ትምርት ገና መስተጋብእ እንደጨረስኍ ትቼው ቅኔ ቤት ገባኍ።[3] ቅኔውን ቅሉ “ሥላሴ” እንደደረስኍ በሥራ ምክንያት የነበረኹበትን ከተማ በመልቀቄ ለመቀኘት ጥቂት ሲቀረኝ አቋረጥኹት። ነገር ግን ከመምህሬ ጉባኤ ብለይም በግሌ ቅኔና ግእዝ ነክ የኾኑ መጻሕፍትን እየገዛኹም እየተዋስኹም አነብ ነበር። አንዳንዴም ሲነሽጠኝ የምቆጥረውን ቅኔ፤ ራሴ በራሴ አላርመው ነገር እየኾነ ቢያስቸግረኝ፤ ዐዲስ አበባ ውስጥ ካንድ ሌላ መምህር ጉባኤ መዋል ጀመርኍ። ነገር ግን ብዙም ሳልቆይ በቂ ጊዜ አገኘኹና ወደመምህሬ ተመልሼ ቤት ሞልቼ ተቀኘኹ። እንዲያውም በዕድሜ ስድስት ዓመት ገደማ የምበልጠው በትምርቱ ግን በዚያን ጊዜም ሙሉ ቤት ያስነግር እና ይዘርፍ የነበረው (አኹን መምህር) ዮሐንስ ጋራ ጓደኝነት ስለመሠረትን አገባብ ጭምር ጥሩ አድርጎ አስተማረኝ። 

እጅግ ጥልቅ ሊቅና ከፍጹም ትሕትና ለሌላ ለማን ተሰጥቶ ይኾን?
አዬ የንታ! ያን ዅሉ ጥበብ ይዘው የሚኖሩባት (መቃብር) ቤት ምን እንደምታኽል እይዋት!

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማናቸውም ግእዝ-ነክ የምርምር ጉዳይ ጠጠር ያለ ነገር ሲያጋጥመኝ የንታንም ኾነ ዮሐንስን መጠየቅ የዘወትር ልማዴ ነው። አዎ፤ ከጉባኤ ተለየኍ እንጂ በፍና ተስእሎ (በጥያቄ መንገድ) የንታም ኾኑ ዮሐንስ እስካኹን ሲስሉኝ ይኖራሉ። (ቀድሞ የቆጠርኹትን ቅኔ እፊቱ ቁሜ ስነግር እጅግ ደሥ ያሰኘኹትና "ጨምር" ብሎ ካንዱ ደረጃ ወደቀጣዩ ያሳለፈኝ እንደኾነ፤ ጕልበቱን ስሜ እግሩ ሥር እቀመጥ እንዳልነበረ፤ ከጊዜ በዃላ ከርሱ እኩል ወንበር ይዤ ለመቀመጥ መድፈሬን በፍና ተሣልቆ (በቀልድ) ቢያስታውሰኝም፤ ከመምህር ዮሐንስ ጋራ ለሻይ ለቡና ስንኳ ዐብረን ከተቀመጥን ነገራችን ኹሉ ያው ግእዝ ነበር። እመለስ ይኾን? አገሬ? ያ ጣዕም እጅግ በጣም ናፈቀኝ!)
ዐይናማው መምህር ዮሐንስ ያን ጊዜ!
አዬ ጨዋታ! አዬ ፈገግታ!
እንዲያ እንዲያ ስል ቆይቼ፤ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገባኍ… በዚኽ መልኩ የቋጠርዃትን ጥቂት ጭብጦ ለማቋደስ መሻቴን ብገልጥላችኍ ብዬ ብዙ ዘበዘብዃችኍ። ይቅርታ።   

እንግዲኽ ሥሯጹ እዚኽ ላይ ይብቃው። ርእሰ ጕዳዩን (ትንሣኤ ግእዝን) የሚመለከተው ዐተታ ግን ይቀጥላል። ትምርቱም በሥራቱ ይጀመራል! ለዛሬ የምትወስዱልኝ መልእክት ጭማቂ፦
አኹን መደንዘዝ ይብቃኝ ብያለኍ። እናም ለመንቀሳቀስ እየጣርኍ ነው። ከምር። ታዲያ ሰው እሻለኍ። የምር ሰው። ባሳቤ ሙሉ በሙሉም ኾነ በከፊል ተስማምቶ (ጭራሽ ሳይስማማስ ቢኾን! እየተሟገቱ መደጋገፍን ምን ይከለክላል? ረ እንዲያውም በከንቱ ውዳሴ ከመላላጥ ይኸ ነው መልካሙ!)፤ ነገር ግን እውነተኛ ማንነቴን፥ ዐይነተኛ አቋሜን ዐውቆ፤ ይልቁንም የእኔን ታናሽነት ሳይኾን የነገሩን ትልቅነት ተገንዝቦ የሚተባበረኝ። በየፈርጁ።ከዅሉም በላይ ጸሎታችኹን እማጠናለኍ።
ይቀጥላል... 


[1] "ለመልአክ ኢናከብሮ ለእመ አሥረጸ ክንፈ በአምጣነ ነዊኅ ቆሙ" እያለ እሚኼድ ቅኔ ነበር። በዚያው አንጻር "ለመምህር ኢናከብሮ ለእመ-ግዋነ ለብሰ በአምጣነ ስፉሕ መትከፉ" ብዬ ጀመርኹና ሙግት ምን ያደርጋል ብዬ ተውኹት...
[2]በእናቴ በኩል አያቴ በሕግ ትዳር መሥርተው ቤት ንብረት አፍርተው ልጆች ወልደው ሲኖሩ ባለቤታቸው ቀድመው ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩኣቸው ቀሪ ዘመናቸውን በምንኩስና ለማሳለፍ ሥራቸውን ትተው ወደገዳም ስለገቡ “አባ” ተብለዋል።
[3] ለዚህ የከፈልኹት ዋጋ፦ 10+1ን ከመላው የሙያ ተማሪዎች አንደኛ ወጥቼ የተሸለምኹት ሰው፤ 10+2 እና 10+3ን ከመላው የሙያ ተማሮች ቀርቶ፤ ከሃያ ከማይበልጡት የክፍሌ ተማሮች ሦስተኛ እና ከዚያም በላይ የምወጣ ኾኘ ነበር፤ ያውም እንደታምር በሚቆጠር ኹናቴ። 10+3ን አጠናቅቄ የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንደወሰድኹ ወዲያውኑ በሙያየ ሥራ ያዝኍ። ሥራውን ከያዝኍ በዃላ የሰማኹት ውጤቴ ለኮሌጅ የሚያበቃ ቢነ(ብ)ብርም ቅሉ፤ ወቅቱ (፲፱፻፹፫ ዓ.ም.) የመንግሥት ለውጥ ያንዣበበበት እና በዚሁም ምክንያት የኮሌጆች ኹኔታ ኹከት የበዛበት ከመኾኑ ጋራ እኔም ደመወዝ ስለቀመስኍ፤ ኮሌጅ የመግባት ዕድሌን አሳላፌው ለዐራት ዓመት ያኽል ግእዝ እና ግእዝ-ነክ በኾኑ ጉዳዮች ላይ የግል ጥናት እያደረግኹ ቆይቻለኍ። ነገር ግን ኮሌጁም አይቅርብኽ ሲለኝ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳው ኮሌጅ ተከፈተና እዚያ ገባኍ... 

2 comments:

  1. እንቋዕ በዳኅና መጻእከ ዳግመ መምህር።ንግባኤከ ሀበ ዘቃዳሚ ነገር ትምህርተ ልሳነ ግእዝ።

    ReplyDelete
    Replies
    1. እወ እኍየ፤ ንግባእኬ ኵልነ...!

      Delete