Saturday, October 8, 2016

“ቤተ ኢትዮጵያ”ን ስለመገንባት

  1. አጭር የታሪክ ማስታወሻ  

ተወደደም ተጠላም፤ እስካኹን ባገራችን ሰፍኖ ያለው “ገዡ መንፈስ” የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው። የተቀረው አንድም ተፎካካሪ ወይም አኩራፊ አለያም ተፃራሪ ነው፤ ኢትዮጵያዊነትን።

አኩራፊና ተፎካካሪዎቹን መናፍስት ለጊዜው ብናቆያቸው፤ ባኹኑ ጊዜ የለየለት የኢትዮጵያዊነት ቀንደኛ ተፃራሪ (ፀረ ኢትዮጵያዊ መንፈስ) የሕወሓት ኢሕአዲግ መንፈስ መኾኑ፤ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ነገር ነው። ርግጥ ነው፤ የዚኽ መንፈስ አገልጋዮች ወይ ከእግዜር አግኝተው ሳይሾሙ፥ አለያም በእውነት ከሕዝብ ሳይመረጡ፤ እንዲያው በሸፍጥ! ቤተ መንግሥት ውስጥ ስለመሸጉና ማናቸውንም የመንግሥት አውታር ስለተቆጣጠሩ፤ ፓርቲኣቸው “ገዡ ፓርቲ” እየተባለ ሲጠቀስ እንሰማለን። ባግባቡም ይኹን ያለአግባቡ “ፓርቲኣቸው” ገዥ ተብሎ ስለሚጠቀስ ብቻ ግን “መንፈሳቸው” ገዥ ነው ለማለት አይቻልም። በፍጹም።

ይኽ ዝንታለም በተፃርሮ የሚኖር “እሱር ወኅሱር” (ተቀፍድዶ የታሰረ እና ሙልጭ ያለ ወራዳ) መንፈስ፤ ላይሳካለት “አግዐዚ ወገዛኢ” የኾነውን (ነጻነት እና ጌትነት ገንዘቡ የኾኑለትን) የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሲታገል ዕድሜውን በሰፍጥ (በሸፍጥ) የጨረሰ “ሰፍጣናዊ” መንፈስ እንጂ፤ “እግዚኣዊ” መንፈስ እንዳይደለ በሚታወቅ ገንዘብ፤ ድርጅቱ ከፅንሱ ጀምሮ እስከ እርጅናው ድረስ ራሱን በራሱ ስንኳ የሚያውቀው በእንቢታ መደብ ነው። (“ወያነ” ወይም “አብዮታዊ” ማለት’ኮ “እንቢታዊ” ማለት ነው)።

“እ[ኽ]ንቢ በል!” የሚሉት ያደግንበት ባህላዊ ሆታ ብቻ ሳይኾን፤ ዃላ በሰከነ መንፈስ የተማርነው “እንብየ በልዎ” (እንቢ በሉት) የሚል የመጽሐፍ ቃል አለና፤ ርግጥ እንቢታ በራሱ ክፉ ነው ለማለት አልችልም። እንቢታ ለማን፤ እንቢታ እስከመቼ፤ ብሎ መጠየቅ ግን አግባብ አለው። እናም፤ ከላይ የጠቀስኩት የመጽሐፍ ቃል ማንን እንቢ ማለት እንደሚገባ በግልጽ አስቀምጦታል፦ “እንብየ በልዎ ለሰይጣን (ለሰፍጣን!)” (ሸፋጩን)፤ ሰይጣንን እንቢ በሉት ነው የሚለው። ሕወሓት ግን፦ “እንቢ ለማን?” ተብሎ ቢጠየቅ፤ የማያሻማ መልሱ “እንቢ ለዐማራ!” ሲኾን፤ “እንቢ ለኢትዮጵያ!” የሚል ጭምር ስለመኾኑም ብዙ ግልጽ ማስረጃዎች ይታያሉ። ይህ እንቢታው በትረ መንግሥትን ጨብጫለኍ ካለ በኋላም መቀጠሉ ደግሞ፤ ይህ ቍራጭ የባንዳ ድርጅት መቸም መች ምሉዕ፥ መቸም መች ገዥ ሊኾን በማይችል በሕጹጽ፥ በሙትቻ መንፈስ እንደሚመራ ምስክር ነው።

ሕወሓት “ትግሬ”ን ነጻ ለማውጣት “እንቢ ለዐማራ” ሲል፤ “ዐማራ” እና “ትግሬ” የተቀረውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ባንድነት “እኛ” የሚሉበትን ገዢውን (የኢትዮጵያዊነት) መንፈስ አክስሞ፤ ኹለቱን በተቃርኖ ማቃወሙ (አንዱ ሌላው ላይ ቀርኑን/ቀንዱን አሹሎ እንዲቆም ማድረጉ) ነው። ከዚህም ጋር የዐማራነት መንፈስ በልዩ ኹናቴ ከነባሩ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተስማማ (የተስተካከለ ላለማለት ነው) ኾኖ ሲታይ፤ እንደ ሸዌው እና እንደ ጎንደሬው እንደጎጃሜው እና እንደ ወሎየው ኹሉ፤ ትግሬም በነባር ኢትዮጵያዊነቱ በተወሰነ መልኩ ዐማራ ኾኖ ስለሚገኝ፤ ያ ኹናቴ እንዳይቀጥል ትግሬነትን ያማራነት ወደረኛ ሲያደርገው፤ ከኢትዮጵያዊነትም ጭምር በተፃርሮ አቁሞታል (“ትግራዋይነት ንጹሕ መንነት” በሚሉት ዐዲስ ዘፈን የሚደለቀው ለዚህ ይመስለኛል!)።

ነገር ግን “ኢትዮጵያ” የምትባለዋ ድንቅ ስም፤ እንዲህ በቀላሉ ተሽቀንጥራ ልትጣል የማትችል ከመኾኑም በላይ፤ ታሪካዊና ባህላዊ መሠረቱን ያልለቀቀ፤ አኹንም ነባር ማንነቱን የጠበቀ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ትግሬ አለና፤ ሕወሓት በትግራይ ውስጥ ሳይቀር ሳይወድ በግዱ በገዡ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንደተረገጠ አለ። መንፈራገጡን ባያቆምም። ክፉ ደዌ

ይህ እንዲህ ነው፤ ይኹንና የሕወሓት መልክ አንድ አይደለም። እንደ ሌታቀን ግምጃ ይለዋወጣል። ተግባሩም እንዲሁ። ከኹሉ የሚገርመው፤ ነባሯን ታሪካዊቷን ኢትዮጵያን አፈራርሶ፤ እንዲያውም ጥንቱን እንዳልነበረች ቆጥሮ፤ ዐዲስ አገር ፈጣሪ ለመኾን (በዓይናማው ዶክተር ዳኛቸው ስላቃዊ አገላለጽ) “ብሔራታ” የሚሉት ዘፈኑን ሲደልቅብን የኖረው ይህ የእኩያን ቡድን፤ ድንገት ተነሥቶ የኢትዮጵያዊነት ጠበቃ ለመምሰል መቃጣቱ ነው። ይኹን እንጂ፤ በሽታው ፈጽሞ ስላልለቀቀው፤ (እንዲያው በስሕተት’ንኳ! ደግ ነገር እንዳያደርግ)፤ በኺደቱ የአንዲቱን አገር፥ የአንዱን ሕዝብ አኩሪ ሥራ በዘር ምዕራፍ ከፋፍሎ የሚያቀርብ የታሪክ አጻጻፍ ስልት (historiography) ፈጥሯል። (ይህም፤ ከሌሎች ጊዜያት በተጨማሪ፤ የሕወሓት ራስ የነበረው መለስ ዜናዊ የዐዲሱን ሚሌኒየም አቀባበል ምክንያት በማድረግ ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ፍልቅቅ ብሎ የወጣ ሲኾን፤ ዃላም ዶክመንታሪ ተሠርቶበታል።) በዚህ የታሪክ አጻጻፍ፤ ቅድመ ክርስትና የነበረውን ለጊዜው ብናቆየው፤ ድኅረ ክርስትና የነበረውን የመጀመሪያውን ሺ (በሕወሓት አስተሳሰብ “መልካም”) ዘመን፦ የትግሬ፤ ከዚያ በኋላ የኾነውን ኹለተኛ ሺ (በሕወሓት አስተሳሰብ “መጥፎ”) ዘመን፦ የዐማራ አድርጎ በመሣል፤ አኹን በሦስተኛው ሺ በተያዘው (የዐማራን አከርካሪ ሰብሮ ቅርሱንም አጥፍቶ) የጥንቱን (“መልካም”) የትግሬ ዘመን የመመለስ ሥራ ላይ እንድንተባበረው (እሱ ራሱ “በጠባቡ” እንደ ዐማራ የሚቆጥረንን ሳይቀር) እየወተወተን ይገኛል። (ድንቅ ነው፤ አእምሮ የሚባል ነገር የተፈጠረብን አይመስላቸውም’ኮ!) የድንቅ ድንቁ ደግሞ፦ ዐውቀውም ይኹን ሳያውቁ አንዳንድ አፈ ጮሌዎች፦ አዎ፤ አኹን ነው እንጂ መልካሙ ዘመን የመጣው፤ ኢትዮጵያ በዓለም “ለመጀመሪያ ጊዜ” የታወቀችበት፤ ዐባይን ልትገድብ ስትነሣ፤ ቅብርጥሶ ቅብርጥሶ እያሉ የ“ልማታ” ዲስኩር በመደስኮር በታሪክ ተሳልቀዋል፤ እየተሳለቁም አሉ።

በርግጥ የኢትዮጵያ ታሪክ በዘር ሳይኾን በዘመን የሚከፋፈልበት እርከን እርከን አለው። ይኹን እንጂ፤ የጥንቱም፥ ያኹኑም የአገሪቱ ታሪክ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እንደጥንቱ ወግ ለመሪዎቹ ሰጥተን እንተርከው ቢባልስ፤ የአኵስምን ሥላጣኔ የመሩት ትግሬዎች ናቸው ያሰኛል እንዴ?

እንደ ፕሮፌሶር ተሻለ ጥበቡ ያሉ ዓይናማ ምሁራን እስከ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ወገን አድርገው “የግእዝ ሥልጣኔ” ይሉታል። ፕሮፌሶር ተሻለ እንዲህ ማለቱ፤ አንዳንድ ጊዜ አገሪቱን ቅሉ “ግዕዝ” ብለው ይጠሯት ከነበሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስተሳሰብ ጋራ ይስማማል (“እስከ ዮም ትትፌሣሕ ወትትሐሠይ ግዕዝ” እንዲል ስንክሳሩ። ይህም ማለት “ግዕዝ [የተባለችው ኢትዮጵያ] እስከ ዛሬ ትደሣለች፤ ሐሴትም ታደርጋለች” ማለት ነው)።

እዚህ ላይ ብዙዎች የማይደፍሩትን ጥያቄ ማንሣት ተገቢ ይኾናል። የእነዚያ አገሪቱን ቅሉ “ግዕዝ” ያሰኛትን ቋንቋ ይናገሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ማንነታቸው “ብሔራቸው”) ማን ነው? ለዚህ ጥያቄ ዝርዝር መልስ ለመስጠት ግን ሰፊ ቦታና ብዙ ጊዜ ስለሚጠይቅ በዚሁ ማለፍ ሳይሻል አይቀርም። “በዚሁ” ማለቴ፤ በጥያቄው ውስጥ ቅሉ መልሱን ባጭሩ ስለጠቆምኍ ነው፤ የለዚያ ሰዎች “ብሔር” ሌላ አይደለም (እንደዛሬዎቹ እንደኛ ማንነት) ያው “ኢትዮጵያዊነት” ነው

ጥቂት ፍንጭ መፈንጠቅ ግን አይከፋም። በእኔ ግምት፤ ጥንቱን አግዓዝያንም ኾኑ ማንም ይጀምረው፤ ግእዝ አንድ ጊዜ የአገሪቱ ዋንኛ ቋንቋ ከኾነ ወዲያ፤ እንደዛሬው ዐማርኛ ከማናቸውም ጎሳ ከማናቸውም ነገድ ይምጣ፤ በትረ ሥልጣን ጨብጦ (በሹመት) የሕዝቡን ሰውነት፥ ትምርት ተምሮ (በዕውቀት) የሕዝቡን አእምሮ፥ ለሰማያዊ አገልግሎት ራሱን ለይቶ (በመንፈሳዊ አባትነት) የሕዝቡን ነፍስ፥ ይገዛ የነበረው የነገሥታት፥ የመኳንንት እና የካህናት ክፍል የሚናገረው ቋንቋ ነበር። ገዥ ቋንቋ ነበር። መንፈሱ አኹንም ገዥ ነው! ሥጋውም ቢኾን ሊቃውንት የግእዝ ብቸኛ አስፈች አድርገው ባቆዩት በዐማርኛ በሌሎቹም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሳይቀር ገዝፎ ይታያል።

በታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘው፤ ባገራችን ከተራው የኅብረተሰብ ክፍል አስቀድሞ ክርስትናን የተቀበለው፤ ክርስቲያን (ዐማራ!) የኾነው፤ ይኸው የነገሥታቱ፥ የመኳንንቱ እና የካህናቱ ክፍል ነው። እንዲህ በመኾኑ በኦሪት ጸንተው የጥንቱን ይሁዲነት መጠበቅ የፈለጉ ወገኖች፤ ጊዜ ጠብቀው በአኵስም ሰፍኖ የነበረውን በኦሪት ላይ ወንጌልን የተቀበለውን የክርስቲያን (የዐማራ) መንግሥት ድል ሲነሡ፤ እነሱ ከጨረሱት የተረፈው ቍጥሩ እጅግ ብዙ የኾነ የመኳንንት እና የካህናት ወገን ሕፃኑን ንጉሥ አንበሳ ውድምን ይዞ ወደ መኻል አገር ሸሽቷል። አስቀድሞም እንጂ፤ ከአንበሳ ውድም በፊት የነበረው ንጉሥ ቅሉ፤ ስፍር ቍጥሩ የትየለሌ የኾነ ሠራዊቱን አስከትሎ ወደደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል፤ በተለይም ያን ጊዜ የተጻፉ የታሪክ መዛግብት “ዐረብ” ይሉት ወደነበረው የዛሬው ቤኒሻንጉል አካባቢ፤ እስከ ሱዳን ጠረፍ ድረስ ዘምቶ እንደነበርና፤ እሱም መኳንንቱና ሠራዊቱም ጭምር በየደረሱበት ተውጠው እንደቀሩ የሚያመለክት ታሪክ አለ። ለዚህም ነበር ዮዲት ጉዲት ማእከላዊ መንግሥቱ በሰሜን በኩል እየተዳከመ መምጣቱን በማየት፤ በአኵስም የነበረውን ወራሴ መንግሥት ሕፃን ንጉሥ አንበሳ ውድምን ከነመኳንንቱ እና ከነካህናቱ አሳድዳ፤ በአካባቢው የነበረውን የክርስትና ምልክት ለማጥፋት የሞከረችው።

ከዮዲት ጉዲት ጥፋት በዃላ አንበሳ ውድም ወደመንበረ መንግሥቱ የተመለሰ ሲኾን፤ ርሱ መዋዕለ ንግሡን ሲፈጽም፤ ዙፋኑን የወረሰው ልጁ ድልነዓድ በነገሠ በሰባተኛ ዓመቱ ማእከሉን ከአኵስም (ከላይ እንደተጠቆመው ቀደም ሲል የነገሥታቱ፥ የመኳንንቱና የካህናቱ ወገኖች በመስፋፋትም በሽሽትም ወደሰፈሩበት) ወደ መኻል አገር እንዳዛወረ ከሌሎች ምንጮች በተጨማሪ በገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ተመዝግቦ ይገኛል (“ወፈለሰት መንግሥት እምአኵስም ኀበ ብሔረ ምስራቅ” እንዲል)። ገድሉ “ብሔረ ምስራቅ” ብሎ የጠቀሰው ዛሬ አምባሰል እየተባለ በሚጠራው አውራጃ የሚገኝ ቦታ ነው። ይኸውም ሊታወቅ፤ ንጉሡ ከሰፈረበት ቦታ ኾኖ የሐይቅን ደሴት አይቶ እንደወደዳት፤ ከአቡነ ሰላማ ዘአዜብ ጋራ በመኾን ደብረ ነጎድጓድ እስጢፋኖስን እንደመሠረተም ተገልጿል። ሐይቅ ደብረ እስጢፋኖስ “ደብረ ነጎድጓድ” የተሰኘበት ምክንያት ቤተ ክህነት እና ቤተ መንግሥቱ በጋራ ስለመሠረቱት እንደኾነ ገድሉ ያስረዳል።

በመቀጠልም ንጉሡ ከደብረ ሐይቅ እስጢፋኖስ በስተቀኝ በኩል በሚገኘው ተራራ ላይ ደብረ እግዚአብሔርን እንደቆረቆረ ይነገራል። በገድሉ እንደምናነበው በዚያን ጊዜ በደብረ እግዚአብሔር ብቻ ስንኳ የሰፈሩት ካህናት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ነበሩ። እነዚህ እንግዲህ ከሚስቶቻቸው እና ከልጆቻቸው ጋራ ቢቆጠሩ ስንት እና ስንት እንደሚኾኑ መገመት ነው። ከዚህም ጋር በተቀሩት አድባራት ኹሉ የተሠሩትን ካህናት ማሰብ ነው። በዚህ ዓይነት የመኳንንቱስ ቍጥር ምን ያኽል ይኾን? የጀሌውስ? (እዚህ ላይ፤ ደብረ እግዚአብሔር ከቤተ ዐምሐራ ቀደምት ማእከላት አንዱ እንደነበር ልብ ይሏል)።

ርግጥ ነው ንጉሡ ድልነዓድ ከዛጔ ሥርወ መንግሥት መሥራቹ ከመራ ተክለ ሃይማኖት ከሸሸ በዃላ፤ ንጉሣዊ ቤተሰቡ ርስት አድርገው የኖሩት ዛሬ ወረኢሉ በሚባለው አውራጃ የሚገኙትን እነ መካነ ሥላሴን እነገነተ ጊዮርጊስን፥ በቦረናም ያሉትን እነ አትሮንሰ ማርያምን እነ ተድባበ ማርያምን ማእከል አድርጎ በመላው ወሎ እና በሸዋ ጭምር ነበር። የዘመኑም ቍጥር የዛጔ ነገሥታት በትረ መንግሥት ጨብጠው ዙፋኑን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ ግራኝ አህመድ እስከተንሣበት ጊዜ ስለሚዘልቅ በትንሹ ግማሽ ሺ ዓመታት ይኾናል።

የዛጔ ነገሥታት አነሣስ በተለያየ መልኩ ይተረካል። ለኔ የተስማሙኝ አንዳንድ ምንጮች እንደሚገልጹት፤ ንጉሡ ድልነዓድ በቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር የሚዘመረው ማሕሌት ለሱ ጭምር እንዲቀርብለት እስከመሻት ደርሶ፤ ፈጣሪውን በትዕቢት ስለተገዳደረ፤ መንግሥቱ ከሱ ተላልፋ ለሴት ልጁ እንድትሰጥ ኾኗል። እንዲህም ስለኾነ፤ ልጁ መሶበወርቅን ባገባው በላስታ ዋግ መስፍን በመራ ተክለ ሃይማኖት አማካይነት መንግሥት ወደ ዛጔ ተዛውሯል። ዛጔ ማለት “ዘአጉየየ” (ንጉሡን) “ያሸሸ” ማለት እንደኽነ የሚገልጹ ምንጮች፤ ከዚሁ ትርጉም ጋራ በሚስማማ ኹኔታ፤ ንጉሡ ድልነዓድ ሸሽቶ ወደ ሸዋ አግጣጫ እንደኼደ ይናገራሉ።

በቅድስናቸው የሚታወቁት የዛጔ ነገሥታት በመንበረ መንግሥቱ በቆዩበት ከሦስት ተኩል ምእት ዓመታት በላይ የሚኾን ዘመን የነበረውን፤ ዃላም የዳዊት/የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ሲመለስ የተሠራውን የቤተ ዐምሐራ ኹናቴ ለማተት ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል። ስለዚህ እንዲያው ባጭሩ በዚህ ከግማሽ ሺ ዓመታት በላይ በተፈጸመው የታሪክ ክስተት፤ ዛሬ ወሎ የተሰኘው ያን ጊዜ ግን ቤተ ዐማራ ተብሎ ይጠራ የነበረው አካባቢ፤ የነገሥታቱ የትውልድ አገር ለመኾን እንደበቃ፤ ዃላ ግን የግራኝን ወረራ ተከትሎ ማእከሉ ወደ ጎንደር እንደተዛወረ በመጠቆም ልለፈው።

ጽሑፌን ከመቋጨቴ በፊት ግን፤ ከቤተ መንግሥቱ በተጨማሪ ስለነበሩት ኹለት ተቋማት አንድ ኹለት ቃል ልጨምር። በዘመኑ ከተጻፉ የታሪክ መዛግብት እንደምንረዳው፤ ያን ጊዜ እንደዛሬው “ቤተ ክህነት” ያለ “ካህናተ ደብተራ” የሚባል በመሠረቱ ሃይማኖታዊ የኾነ ተቋም ነበር። ይህ ተቋም ጥንት ከሌዋውያን ወገን በኾኑ ካህናት መመሥረቱ ተደጋግሞ ይነገርለታል እንጂ፤ ከክርስትና ወዲህ ክህነት በዘር የሚወረስ ባለመኾኑ፤ የዘር ሐረጋቸውን ከሌዋውያኑ የሚመዝዙትም ኾኑ ከማናቸውም ጎሳ የሚወለዱ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ነበር። አዎ የዘር ሐረጋቸው ከየትም ይመዘዝ ከየት፤ ካህናተ ደብተራ ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማገልገል መንፈሳዊ ትምርት አደላድለው ምስጢር አስተውለው በመገኘት፤ በወዲሁም ዓለም ለነገሥታቱ ፍትሕን የሚያመለክቱ ሊቃውንት ስብስብ ነው። ከዚህም ጋር እንደዛሬው ፓርላማ “ዐምሐራ ሠየምት” (ዐማራ ሹማምንት) የሚባል የመማክርት ክፍል እንደነበረ የሚያስረዱ ምንጮች አሉ። ይኸኛውም ቢኾን እንዲሁ ከማናቸውም ጎሳ ተወጣጥተው ነገር ግን የክርስቲያን (የዐማራ) ወገን፥ (ቤተ ዐምሐራ) መኾናቸው የተረጋገጠላቸው መኳንንት ስብስብ ነው። (ያን ጊዜ እሊህ መማክርት ይሰበሰቡበት የነበረው የ“ዐማራ ሳይንት” ስያሜ ቅሉ የተወለደው “ዐምሐራ ሠየምት” ከሚለው እንደኾነ የሚገልጽ ጽሑፍ ማንበቤ ትዝ ይለኛል።)

ይህ እንግዲህ ባገራችን በሚገኙ መዛግብት፥ ማለትም የጽሑፍ መረጃዎች ብቻ ተመሥርቶ መጠነኛ ምርምር በማድረግ ሊደገፍ የሚችል ነው። የታሪካችንን የጊዜ አድማስ በቅጡ ገፋ አድርጎ፤ ቅድመ ክርስትና ከነበረው ዘመን በመጀመር፤ ከአፈ ታሪክ እና ከቍሳዊ መረጃዎች እንዲሁም ከውጭ ጸሐፍያን መዛግብት የሚገኘውን ጭምር በማገናዘብ፤ በጥንተ ታሪክ ምሁራን ጥናት የተደረሰበትን የምርምር ውጤት ግን፤ ዐቅሜ የፈቀደልኝን ያኽል በጥቂቱ የተከታተልኩት ቢኾንም ቅሉ፤ በዚህ ጽሑፍ ልዳስሰው አልሞክርም። ይህንን መሥመር ተከትሎ የሚቀርበውን ዐተታ እንደ ፕሮፌሶር አየለ በከሪ እና ፕሮፌሶር ፍቅሬ ቶሎሳ ጉዳዩን በጥልቀት እና በስፋት ካጠኑት ዓይናማ ምሁራን ገና በደንብ ለመማር እሻለኍ። ታሪክ በየደጁ ይተረካል እንደሚባለው፤ እኔ ግን በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አብነት ተቃኝቶ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ሳይጠራጠሩ ሳይከራከሩ ውድ ገንዘባቸው አድርገው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ቢያንስ በቤተ ክሲያን ሰዎች) አእምሮ ተቀርጾ፤ ያለውን ማኅበራዊ አምሳል (social imaginary) ፈለግ በመከተል ነው ነገሩን እያተትኍ ያለኍት። አምሳል መርገፉ ባይቀርም! (በወዲያው ዓለም! ማለቴ ነው)።

ይቀጥላል…

ድ.ክ. (P.S.)፦ የዚህ ጹሑፍ ዓላማ የተወሰነ ይኅብረተሰብ ክፍል በትልቅነት ቅዥት አብጦ እንዲፈነዳ፤ የተወሰነው ደግሞ በትንሽነት ስሜት ቀጭጮ እንዲማቅቅ ማድረግ አይደለም። የኔ ዓላማ ካኹኑ ችግራችን ጋራ ተያያዥነት ባላቸው ዐይነተኛ ጉዳዮች ላይ ታሪካዊ መሠረታችንን ያልለቀቀ ውይይት ለማድረግና የሚያዋጣ መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችል መነሻ ሐቅ ማስጨበጥ ነው። የሚስተካከለውን ለማስተካከል፤ ዐዲስ ሊሠራ የሚገባውንም ለመሥራት በሐቅ ላይ መመርጎዝ ግድ ነውና።

No comments:

Post a Comment